በታይላንድ እና በካምቦዲያ ድንበር አካባቢ የተቀሰቀሰው ውጊያ ከፍተኛ የሰዎች ሕይወት መጥፋት እና መፈናቀል አስከትሏል።
ከስፍራዉ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በአካባቢው በቀጠለው የከባድ መሳሪያ ተኩስ በርካታ ሲቪሎች እና ወታደሮች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የድንበር ውጥረቱ እንደገና ማገርሸቱ በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ የግዛት ይገባኛል ውዝግብ ያባባሰው ሲሆን፤ በተለይም በጥንታዊ የቤተመቅደስ ቦታዎች ዙሪያ ያለው አለመግባባት ዋነኛው ነዉ ተብሏል፡፡
ውጊያው መጠናከሩን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተፈናቅለው እንዲሰደዱ ሆነዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁኔታው እንዳይባባስ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየጠየቀ ሲሆን፤አንዳንድ ሀገራት እና ድርጅቶችም በሁለቱ ወገኖች መካከል ድርድር እንዲጀመር የሽምግልና ጥረት እያደረጉ ነው።
በማሌዥያ እና በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥረት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበሩት ሁለቱ አገራት ወደ አዲስ ግጭት አምርተዋል።
አንዳቸው ሌላቸውን የተኩስ አቁሙን በመጣስ እየከሰሱም ነው።
ይህ ግጭት ለደቡብ ምስራቅ እስያ ክልል ሰላም እና መረጋጋት አሳሳቢ ስጋት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛሉ እንደ ቢቢሲ ዘገባ።
ሱፊያን አህመድ
ህዳር 30/2018 ዓ.ም
