የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን ማዕከላዊ ግዛት ኮርዶፋን፤ ካዱግሊ በሚገኘው የሎጂስቲክስ ጣቢያው ላይ የተሰነዘረውን የድሮን ጥቃት አዉግዟል፡፡
ጥቃቱ በባንግላዲሽ የሰላም አስከባሪ ቡድን አባላት ላይ ሞትና ጉዳት አስከትሏል ነዉ የተባለዉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሰጡት መግለጫ፤ በሰላም አስከባሪዎች ላይ የሚፈጸሙ እንዲህ አይነት ጥቃቶች ፈጽሞ ተቀባይነት የሌላቸው እና የጦር ወንጀል ሊሆኑ የሚችሉ ናቸዉ ብለዋል፡፡
በጦርነቱ የተሳተፉ አካላት የተመድ ሰራተኞችን እና ንጹሃን ዜጎችን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበው፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ድርጅቱ መረጃ፤ በጦርነት በምትታመሰው ሱዳን ቅዳሜ ዕለት በተመድ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ስድስት ሰላም አስከባሪዎች ተገድለዋል።
በጥቃቱ ሌሎች ስምንት ሰላም አስከባሪዎች ቆስለዋል የተባለ ሲሆን፤ተጎጂዎቹ በሙሉ በአቢዬ ግዛት በሰፈረው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ አስከባሪ ኃይል ውስጥ የሚያገለግሉ የባንግላዲሽ ዜጎች ናቸው።
ጉቴሬዝ፤ በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በአለም አቀፍ ህግ የጦር ወንጀል ሊሆኑ ይችላሉ ያሉ ሲሆን፤ ለዚህ ‹‹ምክንያት አልባ›› ጥቃት ተጠያቂዎች ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
የሱዳን ጦር ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረገው ላለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱን ለመቆጣጠር ከሠራዊቱ ጋር በመዋጋት ላይ ያለውን እና በመጥፎ ስም የሚነሳውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ነዉ፡፡
ነገርግን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።
በ2023 በሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሹ መካከል የተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ በዋና ከተማዋ ካርቱምና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ግልጽ ጦርነት በመቀየሩ ሱዳን ወደ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።
ግጭቱ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል ቢባልም፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ እጅጉን ከፍ ሊል እንደሚችል ይገምታሉ።
በነዳጅ የበለፀገችው አቢዬ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል የምትገኝ አወዛጋቢ ግዛት ስትሆን፤ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነጻነቷን ካገኘችበት ከአዉሮፓዊያኑ 2011 ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ በስፍራው ተሰማርቶ ይገኛል ሲል የዘገበዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።
እስከዳር ግርማ
