ኢዜማ በመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለመሳተፍ መወሰኑን አስታወቀ

“ገዢዉ ፓርቲም ለመጪዉ ምርጫ የመንግስት ስራን እና የፓርቲ ስራን በመለየት፣ የመንግስት ሃላፊነትን ለምርጫ ማስፈጸሚያነት ከመጠቀም ይቆጠብ ሲል” ኢዜማ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ፣ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በመገምገም እና አማራጭ ሀሳቦችን ለህዝብ ለማቅረብ በማሰብ፣ በመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ መወሰኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታዉቋል።

ፓርቲው በመግለጫው እንዳመለከተው፤ ምርጫው የሚካሄድበት ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር፣ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ እና ጽንፍ የረገጠ የፖለቲካ ልዩነት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

ሆኖም ኢዜማ ከትጥቅ ትግል እና ከህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ይልቅ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን እንደ መርህ በመከተሉ፣ ይህንን ምርጫ የህዝብን ይሁንታ ለማግኘት እንደ ብቸኛ አማራጭ ወስዶታል ብሏል።

ኢዜማ አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ሲገመገም፣ በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ የመንግስትን መዋቅር እና ሀብት ለራሱ ፓርቲ መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመሰረታዊ የፖሊሲ አማራጭ ይልቅ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ አጀንዳዎች ላይ ማተኮራቸውን እንደ ችግር አንስቷል።

ምርጫው ነጻ እና ፍትሃዊ እንዲሆን፣ የጸጥታ እና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲያገለግሉ፣ እንዲሁም የመንግስት ሃብት ለገዢው ፓርቲ ቅስቀሳ እንዳይውል ጠይቋል።

በለሌላ በኩል ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህዝብን ከሚያጋጩ ስሜታዊ ቅስቀሳዎች በመውጣት፣ በተጨባጭ የፖሊሲ አማራጮች ላይ የተመሰረተ ክርክር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ለምርጫ ቦርድ ጥሪ ያቀረበዉ ፓርቲዉ የተቋሙን ነጻነት ጠብቆ የምርጫውን ሂደት በብቃት እንዲመራ እና ህጉን እንዲያስከብር ጠይቋል።

ለዓለም አሰፋ

ታህሳስ 07/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *