በሲድኒ ከተማ በአይሁዳውያን ሃኑካህ ክብረ በአል ላይ በተፈፀመ ጥቃት የ15 ያህል ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ሌሎችም ለህይወታቸው አስጊ ሁኔታ ዉስጥ እንደሚገኙ እየተገለፀ ነዉ ።
የአዉስትራሊያ ባለስልጣናት ከዚህ ጥቃት በኋላ የሀገሪቱን የጦር መሣሪያ ህጎች ለማጠናከር ቃል መግባታቸዉን አሶሼትድ ኘሬስ ዘግቧል።
ቀድሞም ጥብቅ ነበር የተባለዉን የሀገሪቱ የጦር መሳሪያ ህግ ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል ነዉ የተባለዉ።
ከሚወሰዱ አዳዲስ እርምጃዎች ዉስጥም የጦር መሳሪያ ብዛትን መገደብ እንዲሁም የተሰጡ ፍቃዶችን መገምገም እንደሆነ የዜና ወኪሉ አስነብቧል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔስ፤ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ለመዉሰድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ለዚህም ጠንካራ የጦር መሳሪያ ህግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ. በ1996 በታስማንያ አንድ ታጣቂ 35 ሰዎችን ከገደለ በኋላ በፍጥነት ተተኳሽ የሆኑ ጠመንጃዎችን ሀገሪቷ ማገዷን ዘገባዉ አስታዉሷል።
ከሰሞኑ በቦንዲ ባህር ዳርቻ የደረሰዉ ጥቃት በአውስትራሊያ ውስጥ በሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት እጅግ አስከፊው ጥቃት ነው ተብሏል።
ጥቃቱን የፈፀሙት አባት እና ልጅ በአውስትራሊያ አስደንጋጭ ማዕበልን የፈጠረ ጥቃትን እንዴት ሊፈጽሙ ቻሉ የሚለዉ እያነጋገረ ነዉ።
ቁምነገር አየለ
ታህሳስ 07/2018 ዓ.ም
