ከዉጪ ገበያ የሚመለሱት ምርቶች ግብይት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አማካኝነት መሆን እንዳለበት ቢቀመጥም ይህ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ተብሏል።
ሁሉም ምርቶች መዳረሻቸዉ እየታወቀ አለመሆኑን የፌደራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ተናገረ። በተለይ የቡና ምርት ለዚህ ተጋላጭ ሆኖ መገኘቱ ነዉ የተገለፀዉ
በትናንትናው እለት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት ቅበላ፣ ክምችት እና የግብይት ሥርዓት አፈፃፀምን በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ማብራሪያ ጠይቋል።
ከዉጪ ገበያዉ የሚመለሰዉን እና የማይወለዉን ምርት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሻጭ እና ገዥን የማገናኘት ሀላፊነት በግብይቱ ላይ እየታየ አይደለም ሲሉ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ገልፀዋል።
አንዳንድ ባለሀብቶች በተለይ የቡና ምርት ከዉጪ ይልቅ የሀገር ዉስጥ ያዋጣቸዋል ያሉት የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ “በትክክለኛው አሰራር ግብይቱ በምርት ገበያዉ በኩል አልፎ እየሄደ ነዉ ወይ ? “ሲሉ ጠይቀዋል።
አያይዘዉም ምርቱ አየር በአየር እየተሸጠ ይገኛል በዚህም መንግስት ከፍተኛ ገቢ እያጣ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ምርት ገበያው ቡና ላኪዎች ለውጭ ገበያ የማይውለውን የቡና ምርት ለተፈቀደላቸው የጅምላ ነጋዴዎች በሚሸጡበት ወቅት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ እንደሚሸጡና እንደማይሽጡ የሚያረጋግጥበት ሥርዓት ዘርግቶ ክትትል የማያደርግ መሆኑ ተረጋግጧል።
ላኪዎችም ቢሆኑ ለውጭ ገበያ የማይውለውን ምርታቸውን ወደ ምርት ገበያው በሚፈለገው ልክ እያመጡ አለመሆኑን በ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀም ግኝት ላይ ተገኝቷል
በምርት ገበያ ከተገኘዉ የክዋኔ ኦዲት ግኝት ዉስጥ የተሰራዉ ትልቁ ግኝት ይሄ እንደሆነ ወ/ሮ መሠረት የገለፁ ሲሆን ትኩረት እንዲሰጠዉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መርጊያ ባይሳ የምርት መሸኛ ሰነድ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ እየተዘጋጀ ነዉ ብለዋል።
ጉምሩክ ኮምሽን በየኬላዉ መቆጣጠር እንዲችል የቡና እና ሻይ ባለስልጣንም የተመለሰዉ እና የተረፈዉ ምርት በአግባቡ ወደ ገበያ እየቀረበ ለሀገር ዉስጥ ፍጆታ እየተገበያየ ነዉ ወይ የሚለዉን እንዲከታተል የመረጃ ልዉዉጥ እንደተጀመረ ተናግረዋል።
ቁምነገር አየለ
ታህሳስ 23/2018 ዓ.ም
