የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዋጋ ንረት መቀነስ ለድሆች የኑሮ መሻሻል ዋስትና እንዳልሆነ አሳሰበ

ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት የመቀነስ ምልክት እያሳየ ቢሆንም፣ የሸቀጦች ዋጋ አሁንም ከፍተኛ መሆኑ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የመግዛት አቅም እያዳከመ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

የድርጅቱ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ ሊ ጁንሁዋ እንደገለጹት፤ የዋጋ ንረት ቁጥር ቢቀንስም አሁንም እየጨመረ የመጣው ከፍተኛ ዋጋ የዜጎችን የመግዛት አቅም እየሸረሸረ ይገኛል።

በመሆኑም ዝቅተኛ የዋጋ ንረት ለቤተሰቦች እውነተኛ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ መሰረታዊ ወጪዎችን መጠበቅ፣ የገበያ ውድድርን ማጠናከር እና ለተደጋጋሚ የዋጋ ንረት መንስኤ የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቧል።

ሪፖርቱ አክሎም ሀገራት የተቀናጀ የገንዘብ፣ የፊስካል እና የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል።በተለይም በምግብ፣ በኢነርጂ እና በሎጂስቲክስ ዘርፎች ላይ የአቅርቦት ሰንሰለትን ማጠናከር ለማህበራዊ መረጋጋት እና ለረጅም ጊዜ እድገት ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት ያለው ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት እና ሀገራት ወደ ራሳቸው ብቻ የማየት ዝንባሌ ለዓለም አቀፍ ችግሮች የጋራ መፍትሄ የመፈለግ መንፈስን እያዳከመው መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

ለዚህም እንደ መፍትሄ የቀረበው የ”ሴቪያ ቃል ኪዳን” የተሰኘው ሰነድ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዋቅርን ለማሻሻል እንደ ፍኖተ ካርታ የሚያገለግል ሲሆን፤ግልጽ የሆነ የብድር አከፋፈል ስርዓት መዘርጋት እና ለታዳጊ ሀገራት የሚቀርበው የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ድጋፍ እንዲሰፋ ይጠይቃል።

ይበልጥ የተረጋጋ እና ፍትሃዊ የዓለም ኢኮኖሚ ለመገንባት በሀገራት መካከል መተማመንን መገንባት እና በህግ ላይ የተመሰረተ የንግድ ስርዓትን ማደስ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጽንኦት ሰጥቷል።

ጥር 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *