ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ ለውጭ ምንዛሪ ሎተሪ ዕድለኞች መኪና እና ሌሎች ሽልማቶችን አበርክቷል፡፡
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ ለሚደረገው ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ ከኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎትና ታሜሶል ኮሚዩኒኬሽን ጋር በመተባበር በኮፔይ ኢ-ብር ሞባይል ዋሌቱ የዲጂታል ሎተሪ ሽያጭ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
ባንኩ ይህን ያሳወቀው ጥር 5፣ 2018 ዓ.ም በዋናው መሥሪያ ቤቱ በተከናወነውና ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ሎተሪ ዕድለኞች የቢ ዋይዲ ሴጉል የኤሌክትሪክ መኪና እና የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክልን ጨምሮ ሌሎች ሽልማቶችን ባበረከተበት ወቅት ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪ የሆኑት አቶ አወሉ አዲሱ ከውጭ የተላከላቸውን ገንዘብ በባንኩ በኩል በመቀበላቸው በ1ኛ ዕጣ የቢ ዋይዲ ሴጉል የኤሌክትሪክ መኪና ሽልማታቸውን ከባንኩ ኦፕሬቲንግ ተጠባባቂ ቺፍ ኦፊሰር አቶ አብዲ ፈቀደ ተቀብለዋል።
በተጨማሪም የአርሲ ዞን ነዋሪው መሐመድ አወል ሐጂ በ2ኛ ዕጣ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል አሸናፊ ሆነዋል፡፡ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በአጠቃላይ በውጭ ምንዛሪ ሎተሪ ለዕድለኞች ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ 63 ሽልማቶች መበርከታቸውን አሳውቋል፡፡
አዲስአለም አበበ
ጥር 05/2018 ዓ.ም
