ይህ ታይዋናዊ ሰው ለ20 ዓመታት ያህል በየቀኑ በአንድ የሙቀት መጠበቂያ ኩባያ (Thermal Mug) ትኩስ ቡና በመጠጣቱ ምክንያት ለሊድ መመረዝ ተጋልጦ በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወቱ አልፏል።
ስሙ ያልተጠቀሰውና በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ይህ ግለሰብ ከ30 ዓመታት በላይ የማሽከርከር ልምድ ነበረው ።
ይሁን እንጂ በማሽከርከር ላይ እያለ በታየበት መዘናጋት መኪናውን ከአንድ ሱቅ ጋር አጋጭቷል።
የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ሰጪዎች ሰውየው ግራ የመጋባት ስሜት ውስጥ ሆኖ አግኝተውታል።
ተከታታይ ምርመራዎች እንደሚያሳዩት ሰውየው በከፍተኛ የደም ማነስ፣ በአንጎል መኮማተር (Cerebral Cortical Atrophy) እና በኩላሊት ሥራ መጓደል ይሰቃይ የነበረ ሲሆን ለተጨማሪ ምርመራም ወደ ኩላሊት ሕክምና ክፍል ሊዘዋወር ችሏል።
የኩላሊት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሁንግ ዩንግ-ህሲያንግ፣ ሰዎች የውኃ መጠጫ ጠርሙሶቻቸውን ወይም የሙቀት መጠበቂያ ኩባያዎቻቸውን በየጊዜው እንዲቀይሩ ለማስጠንቀቅ የዚህን ሰው ታሪክ በታይዋን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ አቅርበውታል።
የሕክምና ቡድኑ የታካሚውን ሁኔታ በሚያጠናበት ወቅት፣ ግለሰቡ በቅርቡ ከፍተኛ ድካምና የምግብ ጣዕም ስሜቱ ተለውጦ ምግብ ላይ ጨው እንደሚያንሰው ይሰማው እንደነበር አውቀዋል።
እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ወደ ሊድ (Lead) መመረዝ የሚያመለክቱ ሲሆን፣ የደም ምርመራውም ይህንኑ አረጋግጧል።
ዶክተሮች የመመረዙን ምንጭ ለማወቅ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት፣ ሰውየው ለ2 አሥርተ ዓመታት ያህል በአንድ የሙቀት መጠበቂያ ኩባያ በየቀኑ ይጠቀም እንደነበር ደርሰውበታል።
የኩባያው ውስጠኛው ክፍል ዝገት ስለነበረው፣ በየቀኑ በሚጠጣው አሲዳማ ቡና ውስጥ ሊድ (Lead) አብሮ ወደ ሰውነቱ ውስጥ ይገባ ነበር።
ሰውየው በመቀጠልም ከዓእምሮ መረሳት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የጤና መታወክ ምልክቶች የታዩበት ሲሆን፣ ጤናውም ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ መሄዱ ተገልጿል።
የመኪና አደጋው ከደረሰ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላም በሳምባ ምክንያት ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
እንደ ፍራፍሬ ጭማቂ፣ ቡና፣ ሻይ እና ባህላዊ የቻይና መድኃኒቶች ያሉ አሲዳማ የሆኑ መጠጦች በአሮጌ ወይም በተበላሹ የሙቀት መጠበቂያ ኩባያዎች ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲቆዩ የከባድ ብረታ ብረት መመረዝ አደጋን ሊጨምሩ ይችላሉ ተብሏል።
ዶክተር ሁንግ ዩንግ-ህሲያንግ በበኩላቸው ሰዎች ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ለመከላከል የኩባያዎቻቸውን ሁኔታ በየጊዜው እንዲፈትሹ መክረዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
ሐመረ ፍሬው
ጥር 08/2018 ዓ.ም
