“15 አጥቂዎች ቢኖሩኝ እንኳ ሞ ሳላህን በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ” አርኔ ስሎት

መሀመድ ሳላህ ከግብፅ ብሄራዊ ቡድን ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ለአንድ ወር ቆይታ ካደረገ በኋላ ቅዳሜ ከናይጄሪያ ጋር የሚደረገውን የደረጃ ጨዋታ አጠናቅቆ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሜርሲሳይድ (ሊቨርፑል) ይመለሳል።

የ33 ዓመቱ ግብፃዊ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ከመሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ በሰጠው አወዛጋቢ ቃለ-መጠይቅ “በክለቡ ውስጥ እኔን የማይፈልገኝ ሰው አለ” ማለቱ እና ከአሰልጣኝ አርኔ ስሎት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው መግለጹ ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት ሊቨርፑል በቻምፒየንስ ሊግ ወደ ጣልያን ተጉዞ ኢንተር ሚላንን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ከቡድኑ ውጪ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ከአራት ቀናት በኋላ ግን ከብራይተን ጋር በነበራቸው የሊግ ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ለጎል የሚሆን ኳስ ማመቻቸት ችሏል።

ለሊቨርፑል በ421 ጨዋታዎች 250 ጎሎችን ያስቆጠረው ሳላህ በዛ ጨዋታ ለክለቡ የመጨረሻ ጨዋታውን አድርጎ ይሁን አይሁን “ምንም ፍንጭ የለኝም” ብለው የነበሩት አሰልጣኝ ስሎት አሁን ግን እሱን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ዛሬ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ፦

“በመጀመሪያ ቅዳሜ ለግብፅ ትልቅ ጨዋታ ማድረግ ይኖርበታል፤ ከዚያም ወደ እኛ ይመለሳል። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሞ ለዚህ ክለብም ሆነ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ተጫዋች ነው። 15 አጥቂዎች ቢኖሩኝም እንኳ እሱን መልሼ በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ምንም እንኳን እርስ በርስ ያለን ግንኙነት እንደበፊቱ ባይሆንም” ብለዋል።

ምስጋናው ታደሰ

ጥር 8/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *