በሱዳን ቀውስ ውስጥ ጾታዊ ጥቃት እንደ ጦርነት መሣሪያ በመዋሉ ሴቶች ‹‹ዋነኛ ሰለባዎች››ሆነዋል ተባለ

የሱዳን ጦር በሚደግፈው መንግስት ውስጥ የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙትና የቀድሞ የመብት ተሟጋች ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት፤በሱዳን ጦርነት ውስጥ ሴቶች የጥቃት ዋነኛ ሰለባዎች ናቸው።

ሴቶቹ የዓለም ‹‹የከፋው››የተባለለትን ጾታዊ ጥቃትና ሌሎች ወንጀሎች ያለጥፋታቸዉ እየተፈጸሙባቸው እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሚያዝያ 2023 ጀምሮ በከባድ ግጭት ውስጥ የቆዩ ሲሆን፤ በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፤ ወደ 11 ሚሊየን የሚጠጉ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
ጦርነቱ በስፋት በሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትም የሚታወቅ ነው።

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ከዝርፊያና ከጥቃቶች ጋር አብረው የሚከሰቱ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፤የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችም ብዙ ጊዜ ቤተሰብ እያየ እንደሚፈጸሙ ሪፖርቶች ያመለክታሉ ብለዋል።

በሙያቸው ሳይኮሎጂስት የሆኑት ሚኒስትሯ፤ምንም ዓይነት የዕድሜ ገደብ የለም፤የ85 ዓመት አሮጊት ልትደፈር ትችላለች፣ የአንድ ዓመት ሕፃንም ልትደፈር ትችላለች ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡

ለረጅም ጊዜ የሴቶች መብት ተሟጋች የነበሩትና በቅርቡ የመንግስት ሹመት ያገኙት ሚኒስትሯ፤ ሴቶች ወደ ጎረቤት አገራት በህገ-ወጥ መንገድ እንደሚሸጡ ገልጸዋል።

ጾታዊ ጥቃት በሁለቱም ወገኖች እንደሚፈጸም ሪፖርቶች ቢኖሩም፤ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዘንድ ግን ጥቃቱ ስልታዊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቡድኑ ጥቃቱን እንደ ጦርነት መሣሪያ እየተጠቀመበት መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከሚያዝያ 2023 እስከ ጥቅምት 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ1 ሺህ8መቶ በላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን መዝግቧል።

ይህ ቁጥር ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በምዕራብ ዳርፉር እና በአጎራባች ኮርዶፋን ክልል የተፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶችን አያካትትም ያለዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።

እስከዳር ግርማ

ጥር 18/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *