በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የግብር ሪፎርሞችና አዳዲስ ሕጎች፣ የመንግሥትን የልማት ገቢ ከማሳደግ ጎን ለጎን የንግዱን ዘርፍ የሚያበረታታ ሊሆን እንደሚገባ የፋይናንስ አማካሪው ጥላሁን ግርማ ተናግረዋል።
በተለይም ለረጅም ጊዜ ኪሳራ የሚያሳውቁ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ታስቦ፣ ማንኛውም ነጋዴ ቢከስር እንኳ ከጠቅላላ ሽያጩ 2.5 በመቶ ግብር እንዲከፍል የሚያስገድደው አዲስ አሰራር፣ ገና በማደግ ላይ ያሉና ትርፍ ባላገኙ አዳዲስ የንግድ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የፋይናንስ ጫና እያሳደረ መሆኑን አብራርተዋል።
የፋይናንስ አማካሪው አቶ ጥላሁን ግርማ መንግሥት ለሀገር ግንባታ የሚውል ገቢ ለመሰብሰብ የሚያደርገው ጥረት የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይሁን እንጂ ሕጎቹ የንግድ ተቋማትን ህልውና በማይጎዳ መልኩ ሊተገበሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የቅሬታ አቀራረብና የይግባኝ ሥርዓቱ ግብር ከፋዩን በሚያበረታታና መተማመንን በሚፈጥር መልኩ ቢቃኝ ለሥርዓቱ ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በመጨረሻም መንግሥት ነጋዴውን በዲጂታል የታክስ አሠራር ላይ የማሠልጠን ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል፣ በጋራ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚሰሩበት ምህዳር ይበልጥ ሊመቻች እንደሚገባ ባለሙያው አመልክተዋል።
ሐመረ ፍሬው
ጥር 19/2018 ዓ.ም
