ሔዝቦላህ እና በኢራቅ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች አሜሪካን አስጠነቀቁ

ባለፉት ሳምንታት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲዝቱ እንደነበረው አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች ኢራንን እንደሚደግፉ ሔዝቦላህ እና በኢራቅ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች አስታወቁ።

በአሜሪካ እና በኢራን መከካል ያለው ውጥረት ዳግም እየበረታ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ የጦር መርከቦች ወደ ቀጣናው መድረሳቸው ተዘግቧል።

ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚል ስጋት የተፈጠረ ሲሆን፣ የሊባኖሱ ሔዝቦላህን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች ጥቃት ከተፈጸመባት ከኢራን ጎን እንደሚቆሙ እየገለጹ ነው።

የሔዝቦላህ ዋና ፀሐፊ ናይም ቃሲም በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት በእነሱም ላይ እንደተፈጸመ የሚቆጠር ገልጸው፤ የአዲስ ጦርነት ነበልባል አጠቃላይ ቀጣናውን የሚለበልብ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የቡድኑ መሪ በተጨማሪም በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ላይ የመግደል ሙከራ “በመካከለኛው ምሥራቅ እና በዓለም መረጋጋት ላይ የሚፈጸም የሽብር ጥቃት” ይሆናል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢራን የሚደገፉ ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች በተመሳሳይ በኢራን ላይ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ከኢራን ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሊባኖሱ ሔዝቦላህ በቅርቡ ከእስራኤል ጋር ገጥሞ በነበረው ጦርነት መሪዎቹን ጨምሮ በርካታ አባላቱ ተገድለውበት ክፉኛ ተዳክሟል። አሁንም ድረስ እስራኤል ወደ ሊባኖስ ዘልቃ በመግባት ቡድኑ ላይ ጥቃት ትፈጽማለች።

ኢራን የፍልስጤሙን ሐማስ እና የየመኑን ሁቲ ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ፀረ አሜሪካ እና እስራኤል የሆኑ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ትታወቃለች እንደ ቢበሲ ዘገባ።

ጥር 20/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *