የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ አዳዲስ ክስተቶችን በትኩረት እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ በሁኔታው ላይ ያላቸውን ጥልቅ ስጋት በይፋ አስታውቀዋል።
ሊቀ-መንበሩ ባወጡት መግለጫ፣ በፌዴራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሃት) መካከል በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በብዙ ጥረት የተገኘ ትልቅ ውጤት መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ ስኬት በምንም መልኩ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደማይገባ አሳስበዋል።
ሊቀ-መንበሩ በማከልም ሁሉም ወገኖች ሁኔታው እንዳይባባስ ከፍተኛ ትዕግስት እንዲያሳዩና በመካከላቸው ያለውን መተማመን ሊያበላሹ ከሚችሉ ማናቸውም ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ማንኛውም ያልተፈቱ ጉዳዮች ካሉም በሰላም ስምምነቱ መንፈስ እና ግዴታዎች መሰረት፣ ገንቢ በሆነ የሰላም ውይይት ብቻ እንዲፈቱ አጥብቀው መክረዋል።
በመጨረሻም፣ የአፍሪካ ህብረት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት በድጋሚ በማረጋገጥ፣ በከፍተኛ የልዑካን ቡድኑ አማካኝነት በወገኖች መካከል መተማመን እንዲገነባ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ለዓለም አሰፋ
ጥር 22/2018 ዓ.ም
