የኑሮ ውድነቱ በዜጎች ላይ የፈጠረው ጫና እንዳለ ሆኖ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚው መስክ አስገራሚ መነቃቃት እያሳየች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
መንግስት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በቢሊየኖች የሚቆጠር ድጎማ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ ባለፉት ስድስት ወራት በታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ አግኝታለች።
በዚህም መሰረት ከሸቀጦች ንግድ 4.5 ቢሊየን ዶላር፣ከአገልግሎት ዘርፍ 4.6 ቢሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ሃዋላ 2.3 ቢሊየን ዶላር፣ እንዲሁም ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ተገኝቷል።
በአጠቃላይ በስድስት ወራት ውስጥ 11.3 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ቤት የገባ ሲሆን፤ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ነው።
በዚህም የተነሳ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ ወደማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የኑሮ ውድነትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ እየፈተነ ስላለው የዋጋ ንረት ሲናገሩ፤ ችግሩ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም እንዲሁም የገቢ መጠን ማነስ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።
መንግስት ይህንን ጫና ለማቅለል በነዳጅ፣ በማዳበሪያ እና በመድሃኒት ላይ በቢሊየኖች የሚቆጠር ድጎማ እያደረገ መሆኑን፣ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን፣ እና የገበያ ስርዓቱን ለማዘመን የእሁድ ገበያዎች እና የዲጂታል ግብይት (ዘመን ገበያ) አማራጮችን በማስፋፋት የደላሎችን ጣልቃ ገብነት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ‹‹ዘመን ገበያ›› በተሰኘው የዲጂታል ግብይት አማካኝነት በአሁኑ ወቅት ከ4መቶ60 በላይ ነጋዴዎች ከ18 ሺህ በላይ የሸቀጥ ዓይነቶችን በቀጥታ ለሸማቹ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ልዑል ወልዴ
ጥር 26/2018 ዓ.ም
