በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከ25 እስከ 30 ሚሊየን ለሚጠጋ ህዝብ አገልግሎት የሚሰጠው የጅማ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማዕከል፤ የህክምና አገልግሎቱን ለማዘመን የሚያስችሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ሊያስገባ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የህክምና ማዕከሉ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሁንዴ አህመድ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ ለታካሚዎች ወሳኝ የሆነውን የኦክስጂን አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያስችል የኦክስጂን ማምረቻ ገንብቶ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ይህም ከዚህ ቀደም ከርቀት ኦክስጂን በሲሊንደር በማጓጓዝ ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጭ የሚያድን ሲሆን፤ ኦክስጂኑ በቧንቧ አማካኝነት በቀጥታ እስከ እያንዳንዱ ታካሚ አልጋ ድረስ የሚደርስ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ማዕከሉ ለራሱ ከሚጠቀመው ባሻገር ለሌሎች የአካባቢው ጤና ተቋማትም ለማዳረስ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም ሆስፒታሉ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቀጥሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለተኛ የሆነውን የአይን ባንክ እና የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም በርካታ የማየት እክል ያለባቸውን ወገኖች ብርሃን መመለስ የተቻለ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ የአይን ብሌን ልገሳ ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ አገልግሎት ታድሶ ወደ ስራ መግባቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ላለፉት ሳምንታት ብቻ ከ40 በላይ ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የሰው ሰራሽ እግር እና እጅ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ዶ/ር ሁንዴ ተናግረዋል፡፡
የህክምና ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ አልጋዎችን ይዞ በዓመት ከ3 መቶ ሺህ በላይ ታካሚዎችን እያስተናገደ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
ጥር 28/2018 ዓ.ም
