በእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር መንግሥት ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ ሎርድ ማንዴልሰን ለአሜሪካ አምባሳደርነት መሾማቸውን ተከትሎ ከእሳቸው ጋር የተለዋወጧቸውን የኤሌክትሮኒክስ መልዕክቶች አሳልፈው ለመስጠት በመዘጋጀት ላይ ናቸው።
ይህ እየተፋፋመ የመጣው ቅሌት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመርን ረቡዕ ዕለት ለጄፍሪ ኤፕስታይን ሰለባዎች ይቅርታ እንዲጠይቁ አስገድዷቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ የጠየቁት የሎርድ ማንዴልሰንን ‹‹ውሸት›› በማመናቸው እና የማንዴልሰንና የህጻናት መድፈር ወንጀለኛ የነበረው የኤፕስታይን ወዳጅነት በይፋ እየታወቀ እርሳቸውን በመሾማቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጥረቱን ለማርገብ ቢሞክሩም አንዳንድ የራሳቸው የፓርላማ አባላት ሳይቀሩ ከሥልጣን እንዲለቁ እየጠየቁ ነው።
የቀድሞው የዳውኒንግ ስትሪት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ጄምስ ሊዮንስ ለቢቢሲ ኒውስ ናይት ሲናገሩ፤የግል መልዕክቶቹ ይፋ መውጣት ተጨማሪ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ወደ ቅሌት ሊጎትት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የሁኔታውን አሳሳቢነት ማንም ሰው አቅልሎ ሊመለከተው አይችልም ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ ቅሌት እ.ኤ.አ በ2009 ከተከሰተው የፓርላማ አባላት የጥቅማጥቅም ቅሌት ወዲህ ትልቁ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ሎርድ ማንዴልሰን በበኩላቸው፤ለአምባሳደርነት ሲታጩ በተደረገላቸው ማጣሪያ ወቅት ስለ ኤፕስታይን የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች በትክክል መመለሳቸውን እንደሚቀጥሉ ታውቋል።
ሆኖም ሰር ኪር ስታርመር ማንዴልሰን ስለ ወዳጅነታቸው መጠን ዋሽተዋል የሚሉ ማስረጃዎችን ይፋ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሀና ሰይፉ
ጥር 29/2018 ዓ.ም
