በሻንጋይ፤ ቻይና የምትኖር አንዲት ሴት የመኖሪያ አካባቢዋ የነበረን የትራፊክ መስታወት ደጋግማ አቅጣጫውን በመቀየር በርካታ የመኪና አደጋዎች እንዲከሰቱ አድርጋለች በሚል ተጠርጥራለች፡፡
ሴትየዋ ይህንን ያደረገችው መስታወቱ የቤቷን ‹‹ፌንግ ሹይ›› ወይንም የመንፈሳዊ ኃይል ፍሰትን አበላሽቶብኛል በሚል እምነት ነው።
ስሟ ያልተጠቀሰው ይህቺ ሴት፤ በቅርብ ጊዜያት ያጋጠማት የጤና መታወክ እና የእድል መራቅ ምክንያት የ‹‹ፌንግ ሹይ››መዛባት ነው ብላ ታምናለች፡፡
ባሏ እንደገለጸው ከሆነ የችግሩን መፍትሄ ለማግኘት የፌንግ ሹይ ባለሙያ አማክረው ነበር በመሆኑም ባለሙያው ከ10 ዓመታት በፊት በቤቷ ፊት ለፊት የተገጠመው የትራፊክ መስታወት ለችግሯ መንስኤ እንደሆነ ነገራት፤ ታዲያ ሴትየዋና ባለቤቷ መስታወቱን በቻይና አፈ ታሪክ ውስጥ ሰይጣንን ለይቶ እንደሚያሳውቅ ‹‹አጋንንት ገላጭ መስታወት›› አድርገው ይወስዱታል።
‹‹እኛ አጋንንት አይደለንም፤ በመሆኑም አጋንንት ገላጭ መስታወት ወደ ቤታችን እንዲያይ አንፈልግም›› ሲል ባለቤቷ ቅሬታውን ለፖሊስ ገልጿል።
ሴትየዋ ማንም ሰው መስታወቱን አይጠቀምበትም ብላ ብትከራከርም ጎረቤቶቿ ግን መስታወቱ ለደህንነታቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የንብረት አስተዳደር ኩባንያው ችግሩን ለመፍታት በመንገዱ ሌላኛው ወገን ላይ ተጨማሪ መስታወት በመግጠም ሴትየዋን ለማስደሰት ሞክሮ ነበር።
ነገር ግን መጀመሪያ ላይ ሴትዮዋ በሀሳቡ ብትስማማም፤ድጋሚ ‹‹እድሌ እየራቀ ነው››ብላ በማሰቧ መስታወቶቹን ማዞር ቀጠለች ይህም በድጋሜ በአካባቢው የመኪና አደጋዎች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆነ።
የአካባቢው ኮሚቴ ሴትየዋን ለማስረዳት ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም፡፡በመጨረሻም ጉዳዩ ለፖሊስ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፤ ፖሊስም መስታወቱን በማዞሯ ምክንያት ለሚደርሱ ማናቸውም የትራፊክ አደጋዎች በህግ እንደምትጠየቅ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷታል።
ፌንግ ሹይ ‹‹ንፋስ እና ውሃ››ማለት ሲሆን፤ የቁሶችን አቀማመጥ እና አቅጣጫ በማስተካከል የኃይል ፍሰትን ለመቆጣጠር የሚረዳ የቻይናውያን ባህላዊ እምነት ነው፡፡
የዚህ እምነት ተከታዮች የቤት ወይም የቁሶች አቀማመጥ በአንድ ሰው ስኬት፣ ጤና እና ደስታ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለው ብለው ያምናሉ ሲል የዘገበው ኦዲቲ ሴንትራል ነው፡፡
ሀና ሰይፉ
የካቲት 05/2018 ዓ.ም
