የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማፋጠን ያለመ ከፍተኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን፣ የአህጉሪቱን የኢንዱስትሪ ልማት እና የ“አጀንዳ 2063” ትግበራን ለማፋጠን ያለመ ከፍተኛ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

በዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት መፍትሄዎች ትብብር (SDSN) አዘጋጅነት በሚካሄደው በዚህ መድረክ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ታዬ አጽቀስላሴን ጨምሮ ታዋቂ የዓለም መሪዎችና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

“የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን በደቡብ-ደቡብ ትብብር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ መድረክ፣ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ስልቶች ላይ ውይይት እየተደረገነ ነው።

ውይይቱ በተለይም በአፍሪካ እና በቻይና መካከል ያለውን አጋርነት ማጠናከር፣ የግሉ ዘርፍ የሚመራውን እድገት ማነቃቃት እና ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆኑ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን በመጠቀም የአህጉሪቱን የንግድ ምንጮች ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል።

በተጨማሪም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ያለውን አቅም ወደ ተግባር በመለወጥ፣ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ሚና ማጎልበት በሚቻልባቸው ተግባራዊ መንገዶች ላይ ጥልቅ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ይህ ከፍተኛ መድረክ የአህጉሪቱን የኢንዱስትሪ መዋቅር ለመቀየር እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚረዱ የፖሊሲ ግብዓቶች የሚገኙበት እንደሚሆንም አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

ልኡል ወልዴ

የካቲት 06/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *