በኤል-ፋሽር በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምርመራ፤ ከተማዋ ለረጅም ጊዜ በተከበበችበት እና በመጨረሻም በቁጥጥር ስር በዋለችበት ወቅት የተፈጸሙ ድርጊቶች እንደ ዘር ማጥፋት ሊቆጠሩ እንደሚችሉ አረጋግጧል።
ምርመራው ትኩረት ያደረገው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተማዋን በተቆጣጠረበት ሁኔታ ላይ ሲሆን፤ ቡድኑ ለ18 ወራት ያህል ምግብ፣ እርዳታ እና የሕክምና አቅርቦቶችን በመከልከል ከተማዋን ከከበበ በኋላ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በቁጥጥር ስር አውሏታል።
መርማሪዎቹ እንደገለጹት፤ በከበባው ወቅት ጥቅም ላይ የዋሉት ስልቶች እና ከተማዋ ከተያዘች በኋላ የተፈጸመው ሰፊ ጥቃት ለይቶ የተወሰኑ ብሔረሰቦች ላይ ያነጣጠረ ሆን ተብሎ የተደረገ ዘመቻ መሆኑን ያመለክታሉ።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ ከሆነ፤ በኤል-ፋሽር የተመዘገቡት የመብት ጥሰቶች ግድያ፣ የፆታ ጥቃት፣ ማሰቃየት፣ በኃይል መሰወር እና ሰብዓዊ እርዳታን ስልታዊ በሆነ መንገድ መከልከልን ያካትታሉ።
ዘገባው እነዚህ ድርጊቶች በዋናነት በዛጋዋ እና በፉር ብሔረሰቦች ላይ ያነጣጠሩ እንደሆኑና ይህም ማኅበረሰቦቹን በሙሉም ሆነ በከፊል የማጥፋት ዓላማ ሳይኖራቸው እንዳልቀረ ከፍተኛ ሥጋትን ፈጥሯል።
ምንም እንኳን ግኝቶቹ እስካሁን መደበኛ የሕግ ውሳኔ ባይሰጡም፤ ሚያዝያ 2023 በሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተፈጽመው ሊሆን እንደሚችል ከተመድ መርማሪዎች እስካሁን የተሰጠው ጠንካራ ማሳያ ነው።
መርማሪዎቹ የኤል-ፋሽር ረጅም ከበባ የፈጥኖ ደራሹ ኃይሎች ወደ ከተማዋ ከመግባታቸው በፊት ለሰላማዊ ሰዎች ለሕይወት አስጊ የሆነ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ወይም መጥፋታቸውን የገለጸው ዘገባው፤ የፈጥኖ ደራሹ ተዋጊዎች በሰላማዊ ሰዎች እና በታጠቁ ተከላካዮች መካከል ልዩነት ሳያደርጉ ጥቃት መፈጸማቸውን ጠቅሷል።
ተልዕኮው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን (ሄሜቲ) ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችን ስም ጠቅሷል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም የቀረቡባቸውን የጅምላ ጭፍጨፋ ውንጀላዎች ውድቅ ቢያደርጉም፤ ስለ ውስጣዊ ተጠያቂነት እርምጃዎች ከመሬማሪዎቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
በተጨማሪም ዘገባው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቁ የውጭ ተዋጊዎች ተሳትፎ እንዳለ ቢጠቁምም፤ድጋፍ እየሰጡ ነው ተብለው የሚታመኑ የተወሰኑ አገራትን ስም አልጠቀሰም።
የተመድ መርማሪዎች አሁን ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዳርፉር ላይ የተጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲያጠናክር፣ ወደ አገር አቀፍ ደረጃ እንዲያሰፋው እና በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አሳስበዋል።
ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጋር የቅርብ ትብብር እንዲደረግ እና ለክስ ሂደቶች ድጋፍ የሚሰጥ ተጨማሪ የፍትሕ ሥርዓት እንዲዘረጋም ጥሪ አቅርበዋል።
እነዚህ ግኝቶች በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውይይቶች ላይ በዋናነት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል አፍሪካ ኒዉስ ዘግቧል።
እስከዳር ግርማ
የካቲት 13/2018 ዓ.ም
