በሜክሲኮ በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈለገውን የዕፅ አዘዋዋሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል በተካሄደ ዘመቻ መገደሉን ተከትሎ በሀገሪቱ የጥቃት ማዕበል ተቀስቅሷል።
‹‹ኤል ሜንቾ››በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው ነሜሲዮ ኦሴጉዌራ ሰርቫንቴስ፤ ጃሊስኮ ኒው ጄኔሬሽን የተባለው አስፈሪ የዕፅ ካርቴል መሪ ነበር።
እሁድ ዕለት በደጋፊዎቹ እና በሰራዊቱ መካከል በተፈጠረ ግጭት በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት መሞቱ ተረጋግጧል።
በመካከለኛው ምዕራብ ጃሊስኮ ግዛት ታፓልፓ በተባለች ከተማ በተካሄደው በዚህ ዘመቻ አራት አባላት የተገደሉ ሲሆን፤ ሦስት የጦር ሠራዊት አባላት ደግሞ መቁሰላቸውን የሜክሲኮ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
የዕፅ አዘዋዋሪው መገደል ያስቆጣቸው ደጋፊዎቹ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ አመጹ ቢያንስ ወደ 12 ግዛቶች የተስፋፋ ሲሆን፤ የቡድኑ አባላት ተሽከርካሪዎችን በማቃጠል መንገዶችን ዘግተዋል።
የፊፋ የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ ከሆኑት ከተሞች አንዷ በሆነችው ጓዳላሃራን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ላይ የጭስ ደመና ሲነሳ የሚያሳዩ ምስሎች በዓይን እማኞች ተቀርፀዋል።
የሜክሲኮ የደህንነት ካቢኔ እንደገለጸው፤ 25 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ከእነዚህም ውስጥ 11ዱ በዓመፅ ድርጊቶች ላይ በመሳተፍ፣ የተቀሩት 14ቱ ደግሞ በዝርፊያ ተጠርጥረው የተያዙ ናቸው።
በዓመጹ ወቅት ሱቆች በእሳት የተቃጠሉ ሲሆን፤20 የሚያህሉ የባንክ ቅርንጫፎችም ጥቃት ደርሶባቸዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሀና ሰይፉ
የካቲት 16/2018 ዓ.ም
