የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓርብ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥለውት የነበረውን ሰፊ የገቢ ዕቃዎች ቀረጥ ውድቅ ካደረገ በኋላ፤ አዲሱ የ10 በመቶ ዓለም አቀፍ ታሪፍ በሥራ ላይ ውሏል።
ባለፈው ሳምንት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከተሰማ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፤ ፕሬዝዳንቱ አዲሱ ቀረጥ ከየካቲት 24 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያዝ የአስፈፃሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ታሪፉን ወደ 15 በመቶ እንደሚያሳድጉ ቢያስፈራሩም እስካሁን ድረስ መጠኑን ለመጨመር የወጣ ይፋዊ መመሪያ የለም።
የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ይህንን ቀረጥ ተግባራዊ እያደረገ ያለው በ1974 የንግድ ሕግ አንቀጽ 1መቶ22 መሠረት ሲሆን፤ ይህም ፕሬዝዳንቱ የኮንግረስን ይሁንታ ሳያገኙ ለ1መቶ50 ቀናት ቀረጥ የመጣል ሥልጣን ይሰጣቸዋል።
የአስፈፃሚ ትዕዛዙ እንደገለጸው፤ ይህ ጊዜያዊ የገቢ ዕቃዎች ቀረጥ ዓላማው ‹‹መሠረታዊ የሆኑ ዓለም አቀፍ የክፍያ ችግሮችን ለመፍታት እና የአሜሪካ ሠራተኞችን፣ ገበሬዎችንና አምራቾችን ለመጥቀም የንግድ ግንኙነቶችን መልሶ የማመጣጠን ሥራን ለመቀጠል››ነው።
ፕሬዝዳንቱ ታሪፎች የአሜሪካን የንግድ ጉድለት ከወጪ ንግድ ይልቅ የገቢ ንግድ የሚበልጥበት መጠን ለመቀነስ አስፈላጊ መሆኑን ሲከራከሩ ቆይተዋል፤ ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት የንግድ ጉድለቱ ከ2024 ጋር ሲነፃፀር በ2.1በመቶ በማደግ አዲስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ይህም በግምት 1.2 ትሪሊየን ዶላር ይሆናል።
ትራምፕ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ‹‹ትርጉም የለሽ፣ በድክመት የተጻፈ እና እጅግ በጣም ፀረ-አሜሪካዊ››ሲሉ አጥብቀው ተችተዋል።
ሰኞ ዕለት፣ ትራምፕ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ በቅርብ የንግድ ስምምነቶች ላይ ‹‹የማጭበርበር ጨዋታ››በሚጫወቱ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ታሪፍ እንደሚጥሉ በድጋሚ አስፈራርተዋል።
ይህ ማስፈራሪያ የመጣው፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሀገራት ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ የትኞቹ ታሪፎች እና የንግድ ስምምነቶች ጸንተው እንደሚቆዩ እየገመገሙ ባሉበት ወቅት ነው።
በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ያለውን የታሪፍ ስምምነት የማታከብር ከሆነ፤ ‹‹ማንኛውም የአጸፋ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል›› ስትል ዩኬ ገልጻለች፤ ሆኖም ‹‹ማንም ሰው የንግድ ጦርነት አይፈልግም››ስትል አክላለች።
የአውሮፓ ኅብረት በበጋው ወቅት የተደረሰውን ስምምነት ማፅደቁን እንደሚያቆም አስታውቋል።
በተመሳሳይ ህንድ በቅርብ የተደረሰውን ስምምነት ለማፅደቅ ቀደም ብለው ተይዘው የነበሩ ንግግሮችን እንደምታራዝም ገልጻለች።
ሀና ሰይፉ
የካቲት 17/2018 ዓ.ም
