የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስቴሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ” እንደ መንግስት እና ፓሊሲ አዉጪ ተቋም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ላለዉ ሁሉ ምላሽ እየሰጠን አንሄድም” ብለዋል።
ሚኒስትሯ እንደገለፁት” ስርአት መዘርጋት አለበት ብለን እናምናለን ፤ እኛ ማህበራዊ አንቂዎች አይደለንም ” ሲሉ ተናግረዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚቀርበዉ የአንድ ሰዉ ወይም የሁለት ሰዉ ኬዝ ሊሆን ይችላል ያሉት ዶ/ር ኤርጎጌ “ሆኖም ያንን እንተወዋለን ማለት አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚገኙ መረጃዎች እንደ አንድ መረጃ ወስደን ወደ ህግ አካላት በማቅረብ የምንሰራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ሚኒስቴሯ አፅንኦት ሰጥተዋል።
” ይህ ማለት ግን እየወጣን መግለጫ የምንሰጥበት አይደለም” ያሉት ዶ/ር ኤርጎጌ ከዲጂታል ስርአቱ ጀምሮ ህጋዊ ስርአቱን ተከትሎ የሚሰራበትን መንገድ እያጠናከርን እንሄዳለን ብለዋል።
“ስርአት ሲገነባ ነዉ ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣዉ ከዚ አንፃር እየሰራን እንገኛለን” በማለት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በግጭት አካባቢዎች ተጋላጭ የሆኑ እና ለጥቃት የተዳረጉ ሴቶች እንዲያገግሙ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል።
ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኢትዮጵያ ከሚፈፀሙ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አንዱ የሆነዉ የሴት ልጅ ግርዛት በ1992 ዓ.ም ከነበረበት 80 በመቶ በ2016 ዓ.ም ወደ 57.8 በመቶ ዝቅ ማለቱን ሰምተናል።
ቁምነገር አየለ
የካቲት 27/2018 ዓ.ም
