እስራኤል በኢራን የነዳጅ ማከማቻዎች ላይ በሰነዘረች ጥቃት፤ የቴህራን ሰማይ ላይ የሚታየው መርዛማ ጭስ ስጋት ፈጥሯል

በእስራኤል እና በኢራን መካከል የሚካሄደው ጦርነት ዘጠነኛ ቀኑን በያዘበት በአሁኑ ወቅት፣ እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ የኢራንን የነዳጅ መሰረተ ልማቶች ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።

ጥቃቱን ተከትሎ የኢራን መዲና ቴህራን በድቅድቅ ጥቁር ጭስ መሸፈኗ ተነግሯል።

የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በኢራን የሚገኙ በርካታ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖዎችን መምታታቸውን ተከትሎ፣ በቴህራን ሰማይ ላይ የተነሳው ጥቁር ጭስ ፀሐይን እስከመጋረድ መድረሱን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

የሮይተርስ እና የኤፒ የዜና ወኪሎች የለቀቋቸው ምስሎች እንደሚሳዩት፣ በመዲናዋ ሰማይ ላይ ታላቅ የጭስ ደመና ተንሰራፍቶ ይታያል።

ይህንን ተከትሎ የኢራን ቀይ መስቀል ማህበር ዛሬ እሁድ ለቴህራን ነዋሪዎች አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

ማህበሩ በመግለጫው፤ ከነዳጅ ዲፖዎቹ የሚወጣው ጭስ መርዛማ እና ለጤና እጅግ አደገኛ በመሆኑ፣ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ከአካባቢው እንዲርቁ አሳስቧል።

ይህ በነዳጅ መሰረተ ልማቶች ላይ የተሰነዘረ ጥቃት፣ ለዘጠኝ ቀናት በዘለቀው በዚህ ጦርነት ውስጥ የመጀመሪያው መሆኑ ተመልክቷል።

ጥቃቱ በኢራን የነዳጅ አቅርቦት እና በኢኮኖሚዋ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ጫና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛሉ።

እስካሁን ባለው መረጃ ጥቃቱ ባደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋት ዙሪያ ከኢራን በኩል የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።

የሁለቱ ሀገራት ፍጥጫ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቅርበት እየተከታተለው ይገኛል።

ልኡል ወልዴ

የካቲት 30/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *