በሪፐብሊክ ኮንጎ የፕሬዝዳንት ዴኒ ሳሱ ንጌሶን የስልጣን ዘመን ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ ሊያራዝም የሚችለው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መጠናቀቁን ተከትሎ የድምፅ ቆጠራ እየተካሄደ ይገኛል።
ምርጫው ትናንት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ይፋዊ ውጤቱ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።
ምርጫው ዝቅተኛ የመራጮች ተሳትፎ የታየበት ሲሆን፤ብዙ ዜጎች የ82 ዓመቱ ዕጩ መሪ ከ40 ዓመታት በላይ ከቆየው አገዛዛቸው በኋላ ምርጫው የፖለቲካ ለውጥ ያመጣል የሚል ጥርጣሬ አላቸው።
በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም በምርጫው ላይ ማዕቀብ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር።
በነዳጅ በበለፀገችው በዚህች የመካከለኛው አፍሪካ ሀገር ስድስት ሌሎች እጩዎች ለፕሬዝዳንትነት ቢወዳደሩም፤ ተንታኞች ግን በኮንጎ ሌበር ፓርቲ ስር ለሚወዳደሩት ሳሱ ንጌሶ ከፍተኛ ፈተና የሚሆን እጩ እንደሌለ ይናገራሉ።
ሳሱ ንጌሶ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣን የያዙት በ1979 ሲሆን፤ ሀገሪቱ የመጀመሪያውን የባለብዙ ፓርቲ ምርጫ እስካካሄደችበት እስከ 1992 ድረስ መርተዋል።
በ1997 ከተካሄደው ሁለተኛው የሪፐብሊክ ኮንጎ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ወደ ስልጣን የተመለሱ ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በስልጣን ላይ ይገኛሉ።
በፈረንጆቹ 2015 የተደረገው የሕገ-መንግስት ሪፈረንደም የፕሬዝዳንታዊ የእድሜ እና የዘመን ገደቦችን በማንሳቱ በድጋሚ እንዲወዳደሩ መንገድ ከፍቶላቸዋል።
ምርጫው እየተካሄደ ያለው ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፍተኛ የመንግስት እዳ እና እየጨመረ የመጣውን የወጣቶች ስራ አጥነት ጨምሮ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ፈተናዎች እየገጠሟት ባለበት ወቅት ነው።
ከ5.7 ሚሊየን የሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በድህነት ውስጥ የሚኖር ሲሆን፤ ወደ ግማሽ የሚጠጋው የህዝብ ቁጥር ደግሞ እድሜው ከ18 ዓመት በታች ነው።
የሳሱ ንጌሶ ድል ከተረጋገጠ፤ እንደ ካሜሩኑ ፖል ቢያ እና የኢኳቶሪያል ጊኒው ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ያሉ ረጅም ዘመን የገዙ የአፍሪካ መሪዎች ስልጣናቸውን አጥብቀው የመያዝ ሰፊ አዝማሚያን የበለጠ የሚያጠናክር ይሆናል።
ሀና ሰይፉ
መጋቢት 07/2018 ዓ.ም
