በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የካንሰር መድኃኒቶችን እና ክትባቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለመሆኑ ተነግሯል።
እስካሁን ሙሉ በሙሉ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ብቻ ጥገኛ የነበረውን የካንሰር መድኃኒቶች እና የክትባት አቅርቦት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑ ተገልጿል።
በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንሲቲትዩት የፋርማሲዩቲካል ኢንድስትሪ ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር መሳይ ወ /ማርያም እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የካንሰር መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ አይመረቱም ብለዋል።
ነገር ግን ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው የአዋጭነት ጥናት መሰረት ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ ገብተው በቂሊንጦ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የካንሰር መድኃኒቶችን በፕሮጀክት ደረጃ ማምረት የሚጀምሩበት ሂደት ላይ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የክትባት ምርትን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ከ72 ዓመታት በፊት በፓስተር ኢንስቲትዩት አማካኝነት እስከ ስድስት የሚደርሱ ክትባቶችን በሀገር ውስጥ ታመርት እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ ሂደት ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ “ኢትዮ ባዮ ፋርማ” በተባለ ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክት አማካኝነት ሀገሪቱ የሚያስፈልጓትን ክትባቶች በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ሰፊ ስራ በቂሊንጦ ፓርክ ውስጥ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህ እርምጃ የሀገሪቱን የጤና ዘርፍ ከውጭ ጥገኝነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያላቅቀው ተጠቁሟል።
ሊዲያ ደሳለኝ
መጋቢት 09/2018 ዓ.ም
