የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው፤ በሱዳን በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት 64 ሰዎች ሲገደሉ 89 ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል።
ከሟቾቹ መካከል 13ቱ ሕፃናት ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንደገለጹት፤ አርብ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት በምስራቅ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ በሚገኘው የኤል-ዳኢን መማሪያ ሆስፒታል ላይ ያረፈ ነው።
“በቂ ደም ፈስሷል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለሦስት ዓመታት ያህል ሱዳንን እያፈራረሰ ያለውን ግጭት ለማቆም ጊዜው አሁን እንደሆነም አክለዋል።
ዶክተር ቴዎድሮስ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሆስፒታሉ ተመትቷል፤ በዚህም 13 ሕፃናት፣ ሁለት ሴት ነርሶች፣ አንድ ወንድ ሐኪም እና በርካታ ታካሚዎችን ጨምሮ ቢያንስ 64 ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።
ኤመርጀንሲ ሎየርስ የተሰኘው የሱዳን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን እንደዘገበው፤ ሆስፒታሉ የተመታው በሱዳን ጦር ሠራዊት ድሮን ነው።
በምዕራብ ሱዳን የሚገኘውን ሰፊውን የዳርፉር ክልል የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወታደራዊ ቡድን ሲቆጣጠረው፤ የሱዳን ጦር ደግሞ የምስራቁን፣ የመካከለኛውን እና የሰሜኑን የአገሪቱን ክፍሎች ይቆጣጠራል።
ዶክተር ቴዎድሮስ እንደገለጹት፤ በጥቃቱ ከቆሰሉት መካከል ስምንቱ የጤና ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ ጥቃቱ የሆስፒታሉን የሕፃናት፣ የወሊድ እና የድንገተኛ አደጋ ክፍሎች አውድሟል።
ሆስፒታሉ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት በአሁኑ ወቅት አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑንና ይህም ‹‹በመሠረታዊ›› የሕክምና አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፍጠሩን ተናግረዋል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
