የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች ለአፍሪካ ህልውና እና ለኢኮኖሚ ጥንካሬ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የዜጎችን ህይወት ለመታደግ አስተማማኝ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን መሰብሰብና መጠቀም ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው “ዛሬን መከታተል – ነገን መጠበቅ” በሚል መሪ ቃል፤ 65ኛው ዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ቀን በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜ እየተከበረ ባለበት  ወቅት ነው።

በኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስተናጋጅነት በተከበረው በዚህ በዓል ላይ፤ የአየር ንብረት መዛባት በአፍሪካ ግብርና፣ በውሃ ሀብት እና በኢነርጂ ዘርፎች ላይ እያደረሰ ያለው ጫና አሳሳቢ መሆኑ ተመላክቷል።

የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት (WMO) ተወካይ በንግግራቸው፤ ትክክለኛ የአየር ንብረት ትንበያ ሊኖር የሚችለው ዛሬ ለሚደረጉ ሳይንሳዊ ምልከታዎች ትኩረት ሲሰጥ ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚያደርጋቸው በረራዎች መረጃዎችን በመሰብሰብ ለዓለም አቀፉ የትንበያ ሥርዓት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ፤ ለዘርፉ ልማት ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በበኩሉ፤ በአህጉሪቱ የሚታዩ ድርቅና ጎርፍ በዜጎች የምግብ ዋስትና ላይ እያደረሱ ያለውን አደጋ ለመቀነስ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን አስታውቋል።

ህብረቱ እስከ 2027 ዓ.ም እያንዳንዱ የአህጉሪቱ ዜጋ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እንዲደርሰው ለማድረግ የያዘው ግብ፤ በአጀንዳ 2063 የተቀመጠውን የአየር ንብረት መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ የመገንባት እቅድ ለማሳካት መሰረት መሆኑ ተገልጿል።

መረጃዎችን ከበረሃ እስከ ጠፈር የሚሰበስቡ ባለሙያዎች፣ ፊኛዎችን በመልቀቅና መረጃዎችን በመተንተን ህይወት የሚታደጉ ሰራተኞች የላቀ ክብር እንደሚገባቸው በዕለቱ ተጠቅሷል።

የቴክኖሎጂ እድገቶች ቢኖሩም፤ የሰው ልጅ አሳቢነትና የባለሙያዎች ክህሎት ለሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ስኬት ቁልፍ መሆኑ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ “ዛሬን መከታተል – ነገን መጠበቅ” የሚለው መሪ ቃል፤ ዛሬ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ለነገው ትውልድ ደህንነትና ለኢኮኖሚ ብልጽግና ዋስትና መሆናቸውን ያመላከተ መሆኑ ተገልጿል።

ልዑል ወልዴ

መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *