በቻይናው ግዙፍ የጭነት መርከብ ድርጅት ኮስኮ የሚንቀሳቀሱ ሁለት ግዙፍ የጭነት መርከቦች ዓርብ ዕለት ሊያደርጉት የነበረውን የመጀመሪያ የጉዞ ሙከራ ካቋረጡ በኋላ፤ በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት መሀል በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል መሻገራቸውን ሰኞ ዕለት ከወጣው የማሪን ትራፊክ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የሁለቱ ግዙፍ መርከቦች ጉዞ ለንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ ሁኔታው ሊቀየር እንደሚችል አመላካች መሆኑን የባህር ላይ ክትትል ተቋሙ በኤክስ ማህበራዊ ገጹ ገልጿል።
ማሪን ትራፊክ ጉዞውን፤ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ በአንድ ትልቅ የጭነት መርከብ የተደረገ የመጀመሪያው የተረጋገጠ ጉዞ ነዉ ሲል ጠቅሶታል።
ይህ ሁኔታ በቤጂንግ እና በቴህራን መካከል አወዛጋቢ በሆነው የባህር መተላለፊያ መብት ላይ የተደረሰ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ሊሆን ይችላል ብሏል።
ኮስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመርከቦች ብዛትና በጭነት አቅም ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ የባህር ላይ ትራንስፖርት ድርጅት ነው።
ኩባንያው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ተለያዩ የባህር ሰላጤ አገሮች የሚያደርገውን የጭነት አገልግሎት አቋርጦ ነበር።
ረቡዕ ዕለት ግን ኮስኮ ከሩቅ ምስራቅ አገሮች ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ባህሬን፣ ኳታር፣ ኩዌት እና ኢራቅ ለሚደረጉ የኮንቴይነር ትራንስፖርት አገልግሎቶች አዲስ ምዝገባ መጀመሩን አስታውቋል።
ለዓለም አቀፍ ንግድ እና ኢነርጂ ቁልፍ በሆነው በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ በእጅጉ ተስተጓጉሏል።
በባህር ወሽመጡ ያለው የነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎል በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ችግር የፈጠረ ሲሆን፤ የነዳጅ ዋጋም እንዲጨምር አድርጓል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 22/2018 ዓ.ም
