የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን አህጉሪቱ እስከ ፈረንጆቹ 2040 ድረስ የ86 ሚሊየን ቶን የነዳጅ እጥረት ሊገጥማት እንደሚችል ገለጸ።
ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው፤ በኢራን ዙሪያ ያለው ጦርነት አህጉሪቱ ለዓለም አቀፍ የባህር ላይ መተላለፊያ መንገዶች ችግር ያላትን ተጋላጭነት አሳይቷል፡፡
አፍሪካ ከምትጠቀመው የተጣራ ነዳጅ ከ70 በመቶ በላይ የምታስገባ ሲሆን፤በየዓመቱ ምግብን፣ ፕላስቲክን፣ ብረታ ብረትን እና ማዳበሪያን ጨምሮ 2መቶ30 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ከውጭ እንደምታስመጣ ሪፖርቱ ጠቁሟል።
በነዳጅ ምርቶች ላይ ያለው የገቢ ንግድ ጥገኝነት በ2023 ከነበረበት 74 ሚሊየን ቶን በ2040 ወደ 86 ሚሊየን ቶን ከፍ ይላል ተብሎ ይገመታል።
ይህ መጠን በናይጄሪያ የሚገኘውና በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የዳንጎቴ ግሩፕ ከሚያንቀሳቅሳቸው ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያዎች የሦስቱንያህል አቅም እንደሆነ ገልጿል።
የሪፖርቱን መውጣት አስመልክቶ በናይሮቢ ንግግር ያደረጉት ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፤በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ቀውስ የዚህን ጥገኝነት መዘዝ ችላ ለማለት የማይቻል እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።
በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስተኛውን የነዳጅ ትራንስፖርት ድርሻ የሚይዘው የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ መዘጋት በገቢ ምርቶች ላይ ጥገኛ የሆኑትን እንደ ምስራቅ አፍሪካ ያሉ ሀገራት ለከፍተኛ የነዳጅ እጥረት እንዲጋለጡ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ይህ የባህር መስመር ለአህጉሪቱ የአቅርቦት መስመሮች ስጋት የሆነ ብቸኛው መተላለፊያ እንዳልሆነም ተገልጿል፡፡
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ፤ጦርነቱ አፍሪካ በሌሎች ላይ ጥገኛ መሆኗን ማቆም እንዳለባት ያሳየ ነው ብለዋል።
ይህ የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋም የአህጉሪቱን የኢነርጂ እጥረት ለመፍታት አዳዲስ የንግድ ማዕከላት መገንባትና ነባር ተቋማት የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
እስከዳር ግርማ
ሚያዚያ 16/2018 ዓ.ም
