ከዛሬ 18 አመት በፊት የቅዱስ ላሊበላን አብያተ ክርስትያናት ጉዳት ለመቀነስ በሚል የተሰራ የብረት መጠለያ ቅርሱን አደጋ ላይ መጣሉ ቢነገርም፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር የብረት መጠለያዉ ቅርሱን ጉዳት ላይ እንደማይጥል ተረጋግጧል አለ

ይህ የብረት መጠለያ በ2000 አ.ም በቤተ መድሃኒያለም እና ቤተ ማርያም ለአምስት አመት ብቻ በሚል የተሰራ እንደነበር ይታወሳል።

በትናንትናው እለት በእንደራሴዎች ምክር ቤት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በምክር ቤቱ ተገኝተው ከአባላት ጥያቄዎች ተጠይቀዋል።

የአንድ ምክር ቤት አባል የዚህን የላሊበላ አቢያተ ክርስቲያን ቅርስ የደህንነት ስጋት የተመለከተ ጥያቄ አንስተዋል።

የምክር ቤት አባሏ በጥያቄያቸዉ ” የብረት መጠለያዉ እንዲነሳ የተቀመጠዉ እና እያገለገለ ያለበት አመት ሶስት እጥፍ እየደረሰ ነዉ። ከዚህ አንፃር ምን እየተሰራ ነዉ?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ለጥያቄዉ ምላሽ የሰጡት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ” ከብረት መጠለያዉ ጥናት ባሻገር አሁን መጠለያዉ ያለበትን ደረጃ ዙሪያ ሳይንሳዊ ምልከታ ሲደረግ ቆይቷል” ብለዋል።

ሚኒስትሯ አክለዉም “እንደሚባለዉ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነዉ ያለዉ ወይስ ያሰብናቸዉን ስራዎች በታቀደለት ሳይንሳዊ ሂደት ለማከናወን የሚያስችል ደረጃ ላይ ነዉ በሚለዉ ዙሪያ ሲሰራ ነበር “ሲሉ ገልፀዋል።

በተደረገዉ ምልከታ አሁን ያሉት የብረት መጠለያዎች እንደሚባለው አደጋ የሚያደርሱ ወይንም እጅግ አንገብጋቢ በሆነ መልኩ ቅርሱን ጉዳት ላይ የሚጥሉ እንዳልሆኑ ተረጋግጧል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ሆኖም የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በጊዜያዊነት ቅርሱን ከዝናብና ፀሐይ ይከልላል በሚል የተሠራው የብረት መጠለያ ሳይነሳ እስካሁንም በመዝለቁ ሌላ ስጋት መፍጠሩን ባሳለፍነዉ አመት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ የነበራቸዉ የቅዱስ ላሊበላ ደብር ዋና አስተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ ተናግረዉ እንደነበር ይታወሳል።

ቁምነገር አየለ

ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *