የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
መቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል በአገሪቱ በሚገኙ 56 ከተሞች ቅርንጫፍ በመክፈት ከ8,500 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን በመንከባከብ ላይ ይገኛል ፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተንከባከባቸው ካለው አጠቃላይ ቁጥር ውስጥ ከ2,500 በላይ የሚሆኑት የአዕምሮ ህሙማን ሲሆኑ፣ ከ3,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የአልጋ ቁራኛ የሆኑና በቀን እስከ ሶስት ጊዜ ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ናቸው።
መቄዶንያ ማህበረሰቡን መሰረት በማድረግ እያከናወነ ባለው በዚህ የሰብዓዊ ተግባር፣ በቀን እስከ 3 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ እያወጣ እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን፣ የስራውን ስፋት ተከትሎ የማህበረሰቡና የመንግስት አካላት ቀጣይነት ያለው ትብብር እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የማዕከሉን ስራ በቅርበት ለመመልከትና ለተደረገው ጥረት ድጋፍ ለማድረግ የፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴርን ጨምሮ የከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ማዕከሉን ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱ በጎ ተግባሩን በማበረታታት ለሌሎች አርአያ እንዲሆንና የማዕከሉን ተልዕኮ ወደ ሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡
አቤል እስጤፋኖስ
ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም
