ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ ምንም ዓይነት መርከብ አላለፈም

ይህ የእንቅስቃሴ መቋረጥ የመጣው በቻይና እና በፈረንሳይ መርከቦች ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት እና ኢራን ለስትራቴጂካዊው የውሃ መስመር ያወጣችውን አዲስ የጉዞ መመሪያ ተከትሎ ነው፡፡

አናዶሉ የባሕር ላይ መርከቦች ክትትል መረጃን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ እስከ ሐሙስ ረፋድ ድረስ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ምንም ዓይነት ዋና ዋና የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ አላለፉም።

ይህም የሆነው የጸጥታ ስጋት በመጨመሩ እና ኢራን በዓለም ላይ እጅግ ወሳኝ በሆነው የባሕር መተላለፊያ ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር በማጥበቋ ነው።

ባለፉት ሳምንታት በወሽመጡ በኩል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ብዙ የመርከብ ድርጅቶች በጸጥታ ስጋት፣ በራዳር ምልክቶች መስተጓጎል እና በመተላለፊያ ሁኔታዎች ላይ ባለው እርግጠኝነት ማጣት ምክንያት ጉዟቸውን እየቀየሩ ይገኛሉ።

የመጨረሻው የእንቅስቃሴ መቆም የመጣው በቤጂንግ የሚገኘው ካይክሲን የተባለ የዜና ወኪል ሰኞ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ የአንድ የቻይና የነዳጅ ጫኝ መርከብ ጥቃት እንደደረሰበት ከዘገበ በኋላ ነው።

ይህ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በቻይና መርከብ ላይ የደረሰ የመጀመሪያው ጥቃት ነው።

ጥቃቱ የተፈጸመው በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አል ጂር ወደብ አቅራቢያ ሲሆን፤በመርከቡ ላይ የእሳት አደጋ አስከትሎ እንደነበር ተገልጿል።

በሌላ በኩል ከምዕራባውያን አገራት ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በአደገኛ ሁኔታ ወሽመጡን ሲያቋርጡ ታይተዋል።

የኢራን ኢስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል እንደገለጸው፤መርከቦች ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያወጣችውን አዲስ የጉዞ ደንብ እያከበሩ ነው።

የባሕር ኃይሉ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት፤ የመርከቦች ትብብር ለቀጣናው የባሕር ደህንነት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንና በአዲሱ መመሪያ መሠረት ‹‹ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተረጋጋ ጉዞ›› እንደሚረጋገጥ ገልጿል።

የባሕር ኃይሉ መርከቦች ኢራን የለየቻቸውን መስመሮች ብቻ እንዲጠቀሙ ያሳሰበ ሲሆን፤ ከመስመር መውጣት እንደ አደገኛ ድርጊት ተቆጥሮ ‹‹ቆራጥ እርምጃ›› ሊወሰድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

የሆርሙዝ ወሽመጥ የፋርስ ባህረ ሰላጤን ከኦማን ባህረ ሰላጤ እና ከአረብ ባህር ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ለዓለም አቀፍ የኢነርጂ ንግድ ወሳኝ የደም ሥር ነው።

የወሽመጡ መስተጓጎል የነዳጅ፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና የተጣራ ነዳጅ ስርጭት ላይ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፤ይህም የዓለም የኢነርጂ ገበያ በግጭቱ ምክንያት ተወጥሮ ባለበት ወቅት የተከሰተ ነው።

ሊዲያ ደሳለኝ

ሚያዚያ 29/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *