በኢትዮጵያ የሚያዝያ ወር 2018 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 11.7 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የስታቲስቲክስ መረጃዎች አመልክተዋል። ይህም ካለፈው መጋቢት ወር የ9.4 በመቶ አኃዝ ጋር ሲነፃፀር የ2.3 በመቶ ጭማሪ የታየበት ሲሆን፣ የኑሮ ውድነቱ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ መቀጠሉን አመላካች ሆኗል።
በሚያዝያ ወር የታየው የምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች የዋጋ ግሽበት 13.5 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በመጋቢት ወር ከነበረበት 11 በመቶ የ2.5 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።
ለዚህ ከፍተኛ ጭማሪ በዋናነት እንደ አትክልት፣ ስጋ፣ የወተት ተዋፅኦዎች፣ እንቁላል፣ ፍራፍሬ፣ የምግብ ዘይትና ስኳር ያሉ መሠረታዊ ሸቀጦች በገበያ ላይ የዋጋ ንረት በማሳየታቸው መሆኑ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበትም በተመሳሳይ በወሩ የ9.1 በመቶ ጭማሪ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ከመጋቢት ወር 7 በመቶ ጋር ሲነፃፀር የ2.1 በመቶ እድገት አሳይቷል።
በዚህ ዘርፍ በተለይም ትራንስፖርት 13 በመቶ፣ አልኮልና ትምባሆ 10.5 በመቶ፣ ኮሙዩኒኬሽን 9.7 በመቶ፣ እንዲሁም ምግብ ቤቶችና ሆቴሎች የ10.5 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል። በተጨማሪም ሌሎች እቃዎችና አገልግሎቶች የ15.9 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ የታየባቸው ዘርፎች ሆነው ተመዝግበዋል ያለው ካፒታል ጋዜጣ ነው።
ሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም
