አሜሪካ እና እስራኤል የቀድሞውን የኢራን ፕሬዝዳንት አህመዲን ነጃድን ወደ ስልጣን ሊያመጡ አቅደው እንደነበር ተገለጸ

ማክሰኞ ዕለት የወጣው የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከፍተው የመጀመሪያ የአየር ድብደባ ካካሄዱ በኋላ የሀገሪቱን የበላይ መሪ አሊ ኻሜኒን በማስወገድ የቀድሞ የኢራን አክራሪ ፕሬዝዳንትን በስልጣን ላይ ለመሰየም አቅደው ነበር።

ይህ ‹‹ደፋር›› የተባለ ዕቅድ በእስራኤላውያን የተጠነሰሰ እና በአሜሪካ መንግስት የጸደቀ ሲሆን፤ዓላማውም የቴህራንን አመራር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጦርነቱ መጀመሪያ ቀናት ባቀረቡት ሃሳብ መተካት ነበር፡፡

ትራምፕ በወቅቱ ከኢራን ውስጥ ያለ ሰው ሀገሪቱን ቢረከብ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመው ነበር።

እንደ ታይምስ ዘገባ ከሆነ ደግሞ ኢራንን ለማስተዳደር የተመረጡት ‹‹ውስጥ አዋቂ ሰው›› ማህሙድ አህመዲን ነጃድ ነበሩ፡፡

ሰውየው ‹‹በእስራኤል እና በአሜሪካ ላይ በነበራቸው አክራሪና ጠንካራ አቋም የሚታወቁ የቀድሞ የኢራን ፕሬዝዳንት›› ናቸው፡፡

የታይምስ ዘገባ አህመዲን ነጃድ እንዴት እንደተመለመሉ ባይገልፅም፤ ከ2005 እስከ 2013 በነበራቸው የፕሬዝዳንትነት ዘመን ‹‹እስራኤልን ከካርታ ላይ ማጥፋት አለብን››በማለት በሚያደርጉት ጥሪ ይታወቃሉ፤ በመሆኑም ይህ ምርጫ ያልተለመደ ምርጫ እንደነበር አመልክቷል።

በተጨማሪም እርሳቸው ‹‹የኢራን የኑክሌር መርሃ ግብር ጠንካራ ደጋፊ፣ የአሜሪካ ከባድ ተቺ እና በሀገር ውስጥ የሚነሱ ተቃውሞዎችን በሃይል በመጨፍለቅ የሚታወቁ››ነበሩ።

ነገር ግን፣ ባለስልጣናቱ ለታይምስ እንደተናገሩት፤ አህመዲን ነጃድን በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን ከቤት እስራት ለማስለቀቅ ታስቦ በተሰነዘረ የእስራኤል የአየር ጥቃት በቴህራን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ላይ በደረሰ ጉዳት ምክንያት የመጀመሪያው እቅድ ሊሰናከል ችሏል።

የአየር ጥቃቱ በታቀደው መሰረት ሳይሄድ ሲቀር አህመዲን ነጃድም ሆኑ የአሜሪካ ባለስልጣናት ‹‹በገዥው አካል ለውጥ ዕቅዱ ላይ ያላቸው ተስፋ መሟጠጡን›› ባለስልጣናቱ አክለው ገልጸዋል።

ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ፤ ከፍንዳታው በህይወት የተረፉት አህመዲን ነጃድ ከዚያ በኋላ በህዝብ ፊት አልታዩም፤ አሜሪካም በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ቦታም ሆነ የጤና ሁኔታቸውን አታውቅም።

ይህ አዲስ የወጣው አሜሪካ እና እስራኤል አህመዲነጃድን የኢራን አዲስ መሪ አድርጎ ለመሰየም የነበራቸው ፍላጎት “የኢራንን የሃይማኖት መንግስት ለመጣል በእስራኤል የተቀነባበረ ባለብዙ ደረጃ እቅድ አካል” እንደነበር ታይምስ የገለጸ ሲሆን፤ ይህም ትራምፕ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግቦቻቸውን ምን ያህል በፍጥነት ማሳካት እንደሚችሉ በተሳሳተ መንገድ መገመታቸውን እና የትራምፕ ረዳቶች ሳይቀሩ ‹‹ሊሆን የማይችል››ብለው በፈረጁት የኢራን አመራር ለውጥ ዕቅድ ላይ ቁማር መጫወታቸውን ያሳያል።

ዋይት ሃውስ እስካሁን ድረስ አህመዲን ነጃድ በገዥው አካል ለውጥ ዕቅድ ውስጥ ስላላቸው ሚና ከታይምስ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም፡፡

ነገር ግን አሜሪካ በኢራን ላይ ስላላት የጦርነት መመሪያ መግለጫ አውጥቷል፤የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ አና ኬሊ በመግለጫቸው፤ ‹ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከመጀመሪያው ጀምሮ ‹‹ኦፕሬሽን ኤፒክ ፉሪ›› በተሰኘው ዘመቻ ላይ ያላቸው ግብ ግልጽ ነበር እሱም የኢራንን ባለስቲክ ሚሳኤሎች ማውደም፣ የማምረቻ ተቋሞቻቸውን ማፍረስ፣ የባህር ኃይላቸውን እና ተላላኪዎቻቸውን ማዳከም ነው” ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ሁሉንም ግቦቹን አሳክቷል፣ አልፎ ተርፎም ከተጠበቀው በላይ ፈጽሟል፤ አሁን ደግሞ ጎረቤቶቻችን የኢራንን የኑክሌር አቅም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስቆም ስምምነት ለማድረግ እየሰሩ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ይህ የኢራንን መሪ የመተካት እቅድ የመጣው በኢራን ላይ ጥቃት ከመሰንዘሩ ከሁለት ወራት በፊት ጥር 3 ቀን የያኔው የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከተጠለፉ በኋላ እና አሜሪካ ከኋይት ሀውስ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሰራ ጊዜያዊ ተተኪ በቀላሉ ማግኘት ከቻለችበት ሁኔታ ማግስት ነበር፡፡

ሆኖም በኢራኑ ጦርነት ወቅት ሁኔታው እንደዚያ አልነበረም፤ አሁን ደግሞ አሜሪካ እና እስራኤል አህመዲን ነጃድን እንዴት ስልጣን ላይ ለመጫን እንዳሰቡ፣ እንዲሁም እሳቸውን አቁስሎ ተልእኮውን ስላከሸፈው እና ስለተበላሸው የአየር ጥቃት ምላሽ ያላገኙ ብዙ ጥያቄዎች አሉ ሲል የዘገበው ኒዉዮርክ ታይምስ ነው።

ሀና ሰይፉ

ግንቦት 12/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *