የፌደራል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጥናታዊ ሪፎርም እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ

በሀገሪቱ የፍትህ ስርዓት ውስጥ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት እና ከጊዜው ጋር የሚራመዱ የህግ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ጥናታዊ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የፌደራል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ከተሰጡት ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ ሲሆን ተቋሙ በየአመቱ በርካታ ጥናቶችን ከማካሄዱ በፊት የፍላጎት ዳሰሳ በማድረግ ዳኞችና የፍትህ አካላትን የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ይለያል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በሶስት ደረጃዎች የተከፈለ የክህሎትና የስነ-ምግባር ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

ለዚህም ማሳያ እንዲሆን በቅርቡ የወጣውን የወንጀል ስነ-ስርዓት ህግና የማስረጃ ህግን በመጥቀስ በውስጡ የተካተቱና ከዚህ በፊት ያልነበሩ በርካታ የተሻሻሉ ጉዳዮችን ዳኞችና አቃቤ ህጎች በየደረጃው አውቀው ስራቸውን በትክክል እንዲሰሩ ለማድረግ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

አምባሳደሩ አክለውም የህግ ባለሙያዎች ከትምህርት ገበታ ሲወጡ የንድፈ ሀሳብ እውቀት ቢኖራቸውም በተግባር የተደገፈ ክህሎት ስለሚያንሳቸው ተቋማቸው በክህሎትና በስነ-ምግባር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው ስልጠናውም በቅድመ-ስራ፣ በስራ ላይ እና በልዩ ስልጠና ደረጃዎች ተከፍሎ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም መሰረት በፍትህ ሚኒስቴር፣ በፍርድ ቤቶች እና በፖሊስ ተቋማት ላይ የተደረገው ጥናት ለመንግስት ከቀረበ በኋላ አሁን ላይ የሚታዩ ከፍተኛ ለውጦች ሊመዘገቡ መቻላቸዉ ተመላክቷል።

ለዓለም አሰፋ

ግንቦት 12/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *