አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የጀመሩትን ጦርነት ሊያቆም የሚችል ስምምነት ይደረሳል በሚል ተስፋ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን፤ የእስያ የአክሲዮን ገበያዎች ደግሞ ጭማሪ አሳይተዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በህንድ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት እንደተናገሩት፤ተደራዳሪዎች “በጠረጴዛው ላይ በጣም ጠንካራ ነገር” እንዳላቸው እና ግጭቱን ለማቆም የሚረዳ ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል ገልጸዋል።
በእስያ ዛሬ ማለዳ የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ መመዘኛ የሆነው ብሬንት በ5.5 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ በአንድ በርሜል 97.90 ዶላር የገባ ሲሆን፥ በአሜሪካ የሚነገደው ድፍድፍ ነዳጅ ደግሞ በ5.9 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ 90.93 ዶላር ሆኗል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ስምምነቱ ቁልፍ የሆነውን የሆርሙዝ ባህረ ሰላጤ የመርከብ ማጓጓዣ መስመርን እንደገና መክፈትን እንደሚያካትት ገልጸው የነበረ ቢሆንም፥ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም።
ከዓለም የነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ውስጥ አንድ አምስተኛ ያህሉ የሚያልፍበት ይህ ጠባብ የውሃ መስመር፥ ግጭቱ ከየካቲት 21 ጀምሮ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ቆይቷል።
ሩቢዮ በህንድ ዋና ከተማ ዴልሂ በሰጡት መግለጫ፤ “አሁንም በሂደት ላይ ያለ ሥራ ነው። ቀደም ሲል እንደተናገርኩት ትላንት ምሽት የተወሰነ ዜና የምንሰማ መስሎን ነበር። ምናልባት ዛሬ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
እሳቸው ይህንን አስተያየት የሰጡት ትራምፕ ቀደም ሲል ስምምነቱ መቃረቡን ጠቁመው የነበረ ቢሆንም፥ በኋላ ላይ ግን ተደራዳሪዎች “ወደ ስምምነት ለመግባት እንዳይቸኩሉ” መመሪያ መስጠታቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው።
ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ከኳታር እና ከሌሎች መሪዎች ጋር “ስለ ሰላም የመግባቢያ ስምምነት “በጣም ጥሩ የስልክ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ትራምፕ “በአሜሪካ፣ በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ እና በተዘረዘሩት ሌሎች የተለያዩ ሀገራት መካከል የመጨረሻ ውሳኔ የሚጠብቅ ስምምነት በአብዛኛው ተደራድሮ አልቋል” ብለዋል።
የስምምነቱ የመጨረሻ ገጽታዎች እና ዝርዝር ጉዳዮች በአሁኑ ጊዜ እየተወያዩበት ሲሆን፤በቅርቡም ይፋ ይሆናሉ፡፡
በተጨማሪም ቅዳሜ ዕለት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና ውይይቱም በጣም ጥሩ እንደነበረ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ስለ ስምምነቱ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፥ ማንኛውም ስምምነት ኢራን የኑክሌር መሣሪያ እንዳታገኝ “በፍጹም” የሚከለክል መሆን እንዳለበት አጥብቀው አሳስበዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኢል ባጋይ፤ ቀደም ሲል ለሀገሪቱ መንግስት ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፤ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ እና የኢራን አቋሞች እየተቀራረቡ የመጡ ቢሆንም፥ ይህ ማለት ግን በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ይደረሳል ማለት እንዳልሆነ አስጠንቅቀው አሜሪካውያንን “ተቃራኒ መግለጫዎችን በመስጠት” ከሰዋል።
ኢራን አሜሪካ እና እስራኤል በሀገሪቱ ላይ ለፈጸሙት ጥቃት የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ የሆርሙዝ ባህረ ሰላጤን ለመጠቀም የሚሞክሩ መርከቦችን እንደምታጠቃ ከዛተች በኋላ፥ ከየካቲት መጨረሻ ጀምሮ በዓለም አቀፍ የኃይል ገበያዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መዋዠቅ ታይቷል።
ምንም እንኳን የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀንስም፥ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ግን አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የላቀ ነው።
ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት ብሬንት በአንድ በርሜል በ70 ዶላር አካባቢ ይነገድ ነበር።
ሀና ሰይፉ
ግንቦት 17/2018 ዓ.ም
