እስራኤል የደቡብ ሊባኖስ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ካሳሰበች በኋላ ጥቃት ሰነዘረች

የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ መሠረተ ልማት ያላቸውን ኢላማዎች በመምታት በደቡብ ሊባኖስ ላይ አዲስ ጥቃቶችን ማድረሱን አስታውቋል።

ባለፈው ረቡዕ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ነዋሪዎች ከድንበር በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ከዛህራኒ ወንዝ በስተሰሜን ወዳለው አካባቢ እንዲሸሹ አሳስቦ ነበር፡፡

እንዲሁም መከላከያ ሰራዊቱ ሄዝቦላህን በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሷል ሲል በመክሰስ “በከፍተኛ ኃይል” እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።

እስራኤል ራሷ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች ሲል የከሰሰው ሄዝቦላህ በበኩሉ፥ ታጋዮቹ ረቡዕ ዕለት ከእስራኤል ወታደሮች ጋር መጋጨታቸውን አስታውቋል።

የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከሆነ፥ ሐሙስ ጠዋት ሁለት የእስራኤል ጥቃቶች በጢግሮስ ከተማ ላይ የተሰነዘሩ ሲሆን፥ ይህም በአንድ ሕንጻ ላይ የእሳት አደጋ አስከትሏል፤ እንዲሁም ከከተማዋ በስተምስራቅ በሚገኝ ሌላ አካባቢ ላይም ጥቃት ደርሷል።

ረቡዕ ዕለት በተላለፈው መልዕክት ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ታዟል፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሚያዝያ 17 ቀን ሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ ይህ ማስጠንቀቂያ ትልቁ ሲሆን፥ ይህም የሊባኖስን 14 በመቶ ግዛት የሚያጠቃልል ነው።

ጥቃቶቹ የተፈጸሙት የሄዝቦላህ ድሮኖች በደቡብ ሊባኖስ በከፊል ይዞታ ላይ በሚገኙ ወታደሮች እና በሰሜን እስራኤል በሚኖሩ ሲቪሎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ፥ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የምድር ጦር ዘመቻውን እንደሚያስፋፉ ካወጁ በኋላ ነው።

በሊባኖስ የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ልዑካን ቡድን መሪ የሆኑት አግነስ ድሁር፥ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ያለው ሁኔታ “ወደ አደገኛ የመጨረሻ ነጥብ እየተቃረበ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

አግነስ ድሁር ሲቀጥሉም “የቀጠለው ግጭት ለሲቪሎች ሊቋቋሙት የማይችሉ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው፤ እንዲሁም የረጅም ጊዜ መዘዞችን ያስከትላል” ብለዋል።

ሀና ሰይፉ

ግንቦት 20/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *