ኔቶ ሮማንያ ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ሰው አልባ አዉሮፕላን መውደቁን ተከትሎ የሩሲያን ‹‹ግድየለሽነት›› አወገዘ

አንድ የሩሲያ ድሮን ሮማንያ ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ተከስክሶ እሳት አደጋ ማድረሱንና ሁለት ሰዎችን ማቁሰሉን ባለሥልጣናት አሳውቀዋል፡፡

ይህም ከኔቶ እና ከአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ጠንካራ ትችትን አስከትሏል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ለክስተቱ በሰጡት ምላሽ፤ የሩሲያ ‹‹የወረራ ጦርነት ሌላ ተጨማሪ ቀይ መስመር አልፏል›› ብለዋል ኔቶ በበኩሉ ‹‹የሩሲያን ግድየለሽነት›› አውግዟል።

በአራት ዓመቱ የዩክሬን ጦርነት ወቅት የሩሲያ ድሮኖች በተደጋጋሚ የሮማንያን ድንበር ጥሰው የገቡ ቢሆንም የኔቶ አባል በሆነችው ሀገር ዜጎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ግን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የሮማንያ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ባለሥልጣን እንደገለጸው፥ የድሮኑ ሙሉ ፈንጂ በመኖሪያ ሕንፃው 10ኛ ፎቅ ላይ በመፈንዳቱ የእሳት አደጋ አስከትሏል።

አሁን ላይ ሁለት ሰዎች አነስተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና እርዳታ እያገኙ ነው በተጨማሪም ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች ከቦታው ተፈናቅለዋል ብሏል።

የሮማንያ መከላከያ ሚኒስቴር ድሮኖቹ ከተገኙ በኋላ ሁለት ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች በአየር ላይ መሰማራታቸውን አስታውቋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ጊዮርጊ ማክሲም እንደተናገሩት፤ ጦር ሠራዊቱ ድሮኑ መኖሩን ካወቀበት ቅጽበት ጀምሮ ሕንፃው ላይ እስካረፈበት ጊዜ ድረስ የነበረው ጊዜ አራት ደቂቃ ብቻ ነበር።

ጄኔራል ማክሲም የሮማንያ ኃይሎች ከፍተኛ እጥረትና ገደብ እንዳጋጠማቸው ገልጸው የዩክሬንን የአየር ክልል የሚጥስ መሳሪያ መተኮስ እንደማይችሉ አስረድተዋል።

‹‹ዩክሬን በጦርነት ላይ ነች፣ ሮማንያ ግን ሰላም ላይ ነች በዚህም ምክንያት ወደ ዩክሬን የአየር ክልል ተተኳሽ መወርወር አንችልም›› ብለዋል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር በደረሰ ሌላ ተመሳሳይ ክስተት አንድ የሩሲያ ድሮን በጋላቲ ከተማ ላይ የንብረት ውድመት አድርሶ የነበረ ቢሆንም ምንም ዓይነት የሰው ጉዳት አልደረሰም ነበር።

የሮማንያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው፥ በዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የድሮን ስብርባሪዎች በሮማንያ ግዛት ውስጥ በ47 የተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ ሲሆን፥ ከነዚህም መካከል 12ቱ የተገኙት በዚህ ዓመት ብቻ ነው።

ሩሲያ እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጠችው ምንም አይነት አስተያየት የለም።

ሀና ሰይፉ

ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *