በትራምፕ እና በኔታንያሁ መካከል የተደረገው ‘እብደት የተሞላበት’ የስልክ ጥሪ  የኢራንን ንግግር አወሳሰበው

ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በሊባኖስ ወታደራዊ እርምጃ ዙሪያ መጋጨታቸው ተሰማ፡፡

ይህ ደግሞ ትራምፕን  ከኔታንያሁ ጋር አለመግባባት ውስጥ የገቡ የመጨረሻው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አድርጓቸዋል። ይህ ግጭት የዋሽንግተንን የኢራን ዲፕሎማሲ ወደ ቀውስ ውስጥ ከቶታል።

ቴህራን እስራኤል በሊባኖስ ላይ ላደረሰችው ጥቃት ምላሽ የሰጠችው ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ንግግር እንደምታቋርጥ በመዛት ሲሆን፣ ይህም ትራምፕ ተወዳጅነት ከሌለው የኢራን ጦርነት እራሳቸውን ለማግለል ለሚያደርጉት ጥረት እክል ሊሆን የሚችል ክስተት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ትራምፕ ሰኞ ዕለት በስልክ ንግግራቸው  ወቅት ኔታንያሁ ላይ “እብድ” በማለት እንደሰደቧቸውና ውለታ ቢስነት እንዳሳዩ ተናግረዋቸዋል  ስለሚለው የአክሲዮስ ዘገባ በአንድ ጋዜጠኛ ተጠይቀው ነበር።

ረቡዕ ዕለት በተሰራጨው የ”ፖድ ፎርስ ዋን” ፖድካስት ቃለ-መጠይቅ ላይ ትራምፕ “አዎ፣ ብያለሁ” ብለዋል። አክለውም “ተቆጥቼ ነበር አልልም። ነገር ግን ሁልጊዜ ከሊባኖስ ጋር በመዋጋቱ ትንሽ ተበሳጭቼ ነበር” ብለዋል።

ትራምፕ “ቢቢን (ኔታንያሁን) በጣም እወደዋለሁ። ከእሱ ጋርም በጥሩ ሁኔታ እሰራለሁ” ሲሉ አክለዋል።

ይህ የቅርብ ጊዜ ግጭት የተሰማው፣ ትራምፕ የአሜሪካ-ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነትን የሚያራዝም እና የቴህራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ለሚደረጉ ንግግሮች በር የሚከፍት ስምምነትን እያሰቡ ባሉበት ወቅት ነው።

ጠቃሚ የአለም አቀፍ የመርከብ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥን መልሶ መክፈትም በዚሁ ስምምነት ላይ የተንጠለጠለ ጉዳይ ነው።

ኔታንያሁ ከአሜሪካዊው ወዳጃቸው ጋር ስላላቸው ውጥረት የተሰነዘረውን ሀሳብ በሳቅ አጣጥለውታል።

ረቡዕ እለት ከሲኤንቢሲ (CNBC) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አንዳንድ ጊዜ፣ በጥሩ ቤተሰቦች ውስጥም እንደሚታየው፣ እንደዚህ አይነት ታክቲካዊ አለመግባባቶች ይኖራሉ” ብለዋል። “ሁልጊዜ የምንፈታበትን መንገድ እናገኛለን፣ እናም ይህን የምናደርገው እንደ ታላቅ ጓደኛሞች ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

እሳቸውና ትራምፕ “ጠዋት ላይ ተኳርፈው” ከሰዓት በኋላ ደግሞ ሊስማሙ እንደሚችሉ አክለው ገልጸዋል።

ግንቦት 27/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *