የቻይና ሰላዮች የቅጥር ወኪል በመምሰል የዩናይትድ ኪንግደም የመንግስት እና የወታደራዊ ሰራተኞችን በማታለል የመንግስትን ሚስጥሮች እንዲያወጡ እያደረጉ መሆኑን ኤምአይ5 (MI5) አስጠንቅቋል።
በዩኬ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ እና በኒውዚላንድ የደህንነት ተቋማት ከተዋቀረው “ፋይቭ አይስ” (Five Eyes) የተባለው የደህንነት ጥምረት በጋራ ባወጣው መግለጫ፤ የቻይና ስውር ወኪሎች እንደ ሊንክድኢን (LinkedIn)፣ ኢንዲድ (Indeed) እና አፕወርክ (Upwork) ያሉ ህጋዊ ድረ-ገጾችን በመጠቀም የሀሰት የትንታኔ (analyst) ስራዎችን እያስተዋወቁ መሆኑን ገልጿል።
ለስራው የሚያመልከቱ ሰዎች በመቀጠል ለህዝብ ይፋ ያልሆኑ “ምስጢራዊ” መረጃዎችን እንዲያጋሩ ጫና ይደረግባቸዋል፤ እነዚህ መረጃዎችም በቻይና ወታደራዊ የስለላ አገልግሎት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ ተብሏል።
“ፋይቭ አይስ” ጥምረት የቻይና ሰላዮች “ለቻይና ስትራቴጂካዊ እና ታክቲካዊ ብልጫ ሊሰጡ የሚችሉ ልዩ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎችን ለማግኘት እንደሚጥሩ” ያስጠነቅቃል።
በዩኬ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ያወገዙ ሲሆን፣ ክሶቹን “ፈጽሞ ውሸት” እና “ተንኮል አዘል ስም ማጥፋት” ሲሉ ገልጸውታል።
ቃል አቀባዩ አክለውም “የፋይቭ አይስ ጥምረት በአለማችን ላይ ትልቁ የስለላ ድርጅት ነው፤ አባላቱም በአለም ዙሪያ በግልጽ የስለላ ስራዎችን ያከናውናሉ። ሰላም ወዳድ ለሆኑ ሀገራት እውነተኛው ስጋት እነሱ ናቸው” ብለዋል።
ጥቃት ሊሰነዘርባቸው የሚችሉ ሰራተኞች የደህንነት ፈቃድ ካላቸው የመንግስት ሰራተኞች ጀምሮ እስከ ምሁራን እና የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ሰራተኞች ድረስ እንደሚጨምር ማስጠንቀቂያው አመልክቷል ያለው ቢቢሲ ነው።
ግንቦት 27/2018 ዓ.ም
ኤምአይ5 (MI5) የቻይና ሰላዮች የመንግስት ሰራተኞችን ለማጥቃት የቅጥር ድረ-ገጾችን እየተጠቀሙ መሆኑን አስጠነቀቀ
