በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ከ418 ሺህ በላይ ህፃናት ለማድረስ ታቅዶ እየተሰጠ ነው።
በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝት ምላሽ ሰጪ ባለሙያ ታደሰ ያለው እንዳሉት÷ ክትባትን በመጠቀም የበለፀገና ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
በሚሰጠው ክትባትም 4መቶ18 ሺህ 5መቶ69 ህፃናትን ለማድረስ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው÷ ክትባቱ በትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ቤት ለቤትና ህጻናት በሚገኙበት አካባቢ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ማሕበረሰቡም በአካባቢያቸው የሚገኙ ህፃናትን በማስከተብ ከበሽታው ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
