ለ10 አመት ሲሰራበት የቆየዉ የታክስ አስተዳደር አዋጅ እንዲሻሻል የማሻሻያ ረቂቁ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቧል።
በትናንትናው እለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የታክስ አስተዳደር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
የዚህ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለግብር ሰብሳቢዉ አካል አቅም የሚሰጥ እና ለግብር ከፋዩ ደግሞ ጫና የሚያሳድር ነዉ በሚል ሲተች መቆየቱ ይታወሳል።
ረቂቅ አዋጅ ከያዛቸዉ ማሻሻያዎች አንዱ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ሽያጭ የፈፀሙ ግብር ከፋዩች ቅጣትን ከ50 ሺህ ብር ወደ 100 ሺህ ብር ከፍ እንዲል የሚያደርገዉ ክፍል ነዉ።
በዚህ አስተዳደራዊ ቅጣት በእያንዳንዱ ደረሰኝ የደረሰኙ ዋጋ ከግምት ዉስጥም የማይገባ መሆኑ አንደኛዉ ቅሬታ ያስነሳ ነጥብም ሆኗል።
በትናንትናው እለት ቋሚ ኮሚቴዉ ባደረገዉ የአስረጂ መድረክ የዋጋ ልዩነት ባላቸዉ ደረሰኞች ግብይት ላይ ተመሳሳይ ቅጣት ማስቀመጥ ቅሬታ ተነስቶበታል።
የሚሊየን አልያም የአስር ብር የንግድ ግብይት ያለ ደረሰኝ የፈፀመ ግብር ከፋይ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የቅጣት መጠን መጣል የፍትሃዊ ቅጣት አጣጣል መርህ ዉጪ ነዉ በሚል በመድረኩ ተነስቷል።
በዚህ ረቂቅ ሰነድ እንደተቀመጠዉ በተመሳሳይ ጥፋት አስተዳደራዊ ቅጣት ተወስኖበት በዓመት ሁለት ጊዜ የተቀጣ እንደሆነ እንዲሁም ሆን ብሎ ድርጊቱን መፈፀሙን ከቀጠለ እና ከታወቀ ድርጊቱ እንደ ወንጀል ጥፋት ተቀጥሮ በወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነ ያሳያል።
በአስረጂ መድረኩ ተገኝተዉ የነበሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የህግ አማካሪዉ አቶ ዋሲሁን አባተ እንደገለፁት” በኢትዮጵያ የታክስ አስተዳደር ስርአት ዉስጥ ፈታኙ ነገር ደረሰኝ ነዉ” ብለዋል።
ይህ የተቀመጠዉ ቅጣት የአሰራር ጥሰቱ ላይ እንጂ የሽያጭ መጠኑ ላይ ትኩረት የሚያደርግ አይደለም በሚል የመከራከሪያ ነጥብም አንስተዋል ።
ደረሰኝ ሳይቆርጡ መገበያያ ድርጊት እየባሰበት መጥቷል ያሉት አማካሪዉ ሁለት ጊዜ የተቀጣ ግብር ከፋይ ድርጊቱ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የሚወሰድ መሆኑን ተከትሎ ቅጣት እንዴት ነዉ የሚጣለዉ የሚለዉን በተመለከተ “በተቀመጡት የቅጣት መጠን ዉስጥ እንዴት አድረጌ ልቅጣ የሚለዉ የዳኞች ስራ ነዉ” ሲሉ አቶ ዋሲሁን ተናግረዋል።
በአዋጁ ዙሪያ የፊታችን ሰኞ የሕዝብ ማድመጫ መድረክ (Public Hearing) እንደሚኖር ቋሚ ኮሚቴዉ አስታውቋል።
ቁምነገር አየለ
ሰኔ 04/2018 ዓ.ም
