የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ፤በሊባኖስ ላይ የሚሰነዘሩ የእስራኤል ጥቃቶች መቆምን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ጦርነት ማብቃቱ በኢራን እና በአሜሪካ-እስራኤል መካከል ያለውን ጦርነት ለማቆም ‹‹ቅድመ ሁኔታ›› ነው ብለዋል።
አራግቺ በዋና ከተማዋ ቴህራን ለተሰበሰቡ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ልዑካን እንደገለጹት፤ የሊባኖስ እና የኢራን ግንባሮች በሆነ መልኩ የተሳሰሩ እና እርስ በርስ ጥገኛ ሆነዋል።
ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በሊባኖስ ያለውን ጦርነት ማቆም ከኢራን ጋር ያለውን ጦርነት ለመጨረስ እንደ ቅድመ ሁኔታ ቆጥራዋለች።
አሁን የጦርነቱ ማብቂያ ላይ ስለደረስን፣ በሊባኖስም ጦርነቱ ያበቃል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሊባኖስ የሚደረገውን የተኩስ አቁም በቅርቡ ከአሜሪካ ጋር ከተደረሰው ስምምነት ‹‹የማይነጠል›› አካል እንደሆነ ገልጸዋል።
በስዊዘርላንድ ዓርብ ዕለት የሚጀመረው የአሜሪካ እና የኢራን ውይይት በሁለት ምዕራፎች እንደሚከፈል አራግቺ መናገራቸውን ታስኒም የተባለው የኢራን የዜና ወኪል ዘግቧል።
እንደ አራግቺ ገለጻ፤የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆርሙዝ ወሽመጥን፣ የባሕር ላይ ገደቦችን እና ከጦርነት በኋላ ያለውን የኢራን የመሠረተ ልማት መልሶ ግንባታ ጉዳዮችን የሚመለከት ሲሆን፤ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በመጨረሻ ስምምነት ላይ በሚወሰኑ የኒውክሌር ጉዳዮች እና የማዕቀብ ማቃለያዎች ላይ ያተኩራል።
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 09/2018 ዓ.ም
