ቦርዱ የፓርቲውን ጥያቄ ሳይቀበለው የቀረው ቅሬታው በበቂ ማስረጃ ባለመደገፉ ነው ብሏል።
ፓርቲው በበኩሉ የተፈጸመው የምርጫ ሕግ ጥሰት የጣት አሻራን ጨምሮ በፎረንሲክ ምርመራ እንዲጣራ ያቀረብኩትን ጥያቄ ቦርዱ ተፈጻሚ አላደረግም ሲል ወቅሷል።
ቦርዱ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ለፓርቲው በጻፈውና የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ እንግዳሸት በፈረሙበት ይፋዊ ደብዳቤ፤ ፓርቲው ያቀረበው ቅሬታ በቂ ማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ በበኩሉ አቤቱታውን ተከትሎ የተባለውን የምርጫ ሕግ ጥሰት ለማጣራት አጣሪ ኮሚቴ በማደራጀት ሂደቱን ሲያጠና፣ ሲያመራምር እና ሲመረምር መቆየቱን በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል።
ሆኖም ቦርዱ ባደረገው ማጣሪያ “ፓርቲው ያቀረበው ቅሬታ በበቂ ማስረጃ ያልተደገፈ ሆኖ ተገኝቷል” በሚል ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉንና ውሳኔውን ለፓርቲው ማሳወቁን ገልጿል። ቦርዱ የዚህን ውሳኔ ግልባጭ በቁጫ ምርጫ ክልል በዋና ተፎካካሪነት ለተወዳደረውና ይኸው ውሳኔ ለሚመለከተው ለገዢው ብልፅግና ፓርቲም ልኳል።
የቅሬታው መነሻ «በቁጫ ምርጫ ክልል የምርጫ ሕግን የተላለፉ፣ የመራጮችን ነጻነት እና ምስጢራዊነት የጣሱ ድርጊቶች ተፈጽመዋል የሚል ነው። በዚህም ምክንያት «በቁጫ ምርጫ ክልል የተካሄደው ምርጫ እንዲሰረዝ » ሲል ነበር ፓርቲው ጥያቄውን ለቦርዱ ያቀረበው።
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እጩዎቹን አቅርቦ የተወዳደረው በጋሞ ዞን ቁጫ ምርጫ ክልል ነው።
ፓርቲው በምርጫው ላይ ታይተዋል ያላቸውን የምርጫ ሕግ ጥሰቶች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታውን ያቀረበው ባለፈው ግንቦት 24 የተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ተከትሎ ነበር።
ምርጫ ቦርድ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዳልተቀበለው የጠቀሰው ፓርቲው ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንደሚወስድ አስታውቋል።
ሰኔ 10/2018 ዓ.ም
