ዛሬ ማለዳ በደቡብ ሊባኖስ ናባቲህ ከተማ እና በአካባቢው ባሉ ከተሞች ላይ እስራኤል በፈጸመችው የቦምብ እና የመድፍ ጥቃት ቢያንስ 24 ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው እና እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት እንዲቆም የሚያዝዘው ስምምነት ተግባራዊ ቢሆንም፤ከእኩለ ሌሊት በኋላ በእስራኤል የተፈጸሙ ጥቃቶች በናባቲህ አውራጃ ውስጥ በሚገኙት አል-ሻርቂያ፣ ሀሩፍ እና ክፋር ሲር ከተሞች የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶችን ኢላማ አድርገዋል።
በዚህም ሳቢያ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የደረሱበት እንዳልታወቀ ተዘግቧል።
ረቡዕ ምሽት የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን፤ በአሜሪካ እና በእስራኤል በኢራን ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለማቆም እና እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለመግታት ያለመውን ‹‹የኢስላማባድ የመግባቢያ ስምምነት››በኤሌክትሮኒክ መንገድ ፈርመዋል።
በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት ዋሽንግተን እና ቴህራን በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር እና በአለም አቀፍ ማዕቀቦች ላይ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ለ60 ቀናት የሚቆይ እና ሊራዘም የሚችል ድርድር ያደርጋሉ።
እስራኤል ከመጋቢት 2 ጀምሮ በሊባኖስ ላይ ባካሄደችው ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት እስካሁን 3 ሺህ9መቶ12 ሰዎች ሲገደሉ፤ 11 ሺህ 8መቶ73 ቆስለዋል እንዲሁም ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸውን የቅርብ ጊዜ መረጃ ያሳያል፡፡
እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎችን ለአሥርት ዓመታት፤ሌሎችን ደግሞ ከቅርብ ጊዜው ግጭት ወዲህ መያዟን ቀጥላለች።
በቅርቡ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ የእስራኤል ጦር ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ሊባኖስ ግዛት ዘልቆ መግባቱ ተገልጿል።
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 12/2018 ዓ.ም
