‹‹መንግስት የቴክኖሎጂ አማራጮችን ሊያበረታታ ይገባል›› አቶ ሳምሶን ከተማ የኢትዮጵያ ፕላስቲክ እና ጎማ አምራቾች ማህበር ስራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የአንድ ጊዜ አገልግሎት ፕላስቲኮች እገዳ ለህብረተሰቡና ለአምራቾች በቂ አማራጭና የሽግግር ጊዜ ሳይሰጥ በመተግበሩ በገበያውና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ክፍተትና አለመረጋጋት መፍጠሩን የኢትዮጵያ ፕላስቲክ እና ጎማ አምራቾች ማህበር አስታወቀ።

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን ከተማ ፥የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ያወጣውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው አዋጅ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል አስፈላጊ መሆኑን ማህበሩ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ ገልጸው፤የህግ አውጪው አካል ህጉን ከማውጣቱ በፊት የህብረተሰቡን ተጨባጭ ሁኔታ እና አማራጮችን በሚገባ ማጥናት እንደነበረበት አንስተዋል።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ፥ ቀደም ሲል ከ0.03 ማይክሮን በታች የሆኑ ስስ ፕላስቲኮች ብቻ ተከልክለው ነበር፡፡

በአዲሱ አዋጅ ግን የገበያ መያዣዎችን ጨምሮ ሁሉም የአንድ ጊዜ አገልግሎት ፕላስቲኮች ሙሉ በሙሉ ታግደው፥እንደ ባልትና መያዣዎች ያሉ የተወሰኑ የፕላስቲክ አይነቶች ከእገዳው ውጪ ተደርገዋል ብለዋል።

በአዲሱ አሰራር በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ ከባድ ፈተና መደቀኑን የገለጹት አቶ ሳምሶን፥ በአማራጭ እጥረትና የሽግግር ጊዜ ማነስ ምክንያት አብዛኞቹ የማህበሩ አባላት ማሽኖቻቸውንና ስራቸውን ወደ ሌላ ምርት ለመቀየር በቂ ጊዜ አላገኙም ብለዋል።

በእገዳው ሳቢያ ስራቸውን ሙሉ በሙሉ ያቆሙ እና ወደ ሌላ ዘርፍ የተሸጋገሩ አምራቾች መኖራቸውንም አንስተው፤የገበያውን ፍላጎት ተከትሎ አንዳንድ አምራቾች ወደ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመግባት መገደዳቸውንም ጠቁመዋል።

ስራ አስኪያጁ ‹‹መንግስት ከደፈና እገዳ ይልቅ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ሊያበረታታ ይገባል›› ብለዋል።

መንግስት የኢንዱስትሪውንና የአካባቢውን ደህንነት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስቀጠል እንዲችል በአጭር ጊዜ ውስጥ መሬት ላይ ሊበሰብሱ የሚችሉ ፕላስቲኮችን በማምረት አምራቾች ወደነዚህ የቴክኖሎጂ አማራጮች እንዲሸጋገሩ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እገዳው ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ሰብስቦ መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራዎችን በስፋት መስራት እንደሚገባ ማህበሩ በጥብቅ አሳስቧል።

ሀና ሰይፉ

ሰኔ 22/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *