የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የሰረቀው ግለሰብ በ6 ዓመት ፅኑ እስራት ሲቀጣ፤ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰው ድርጅት ደግሞ ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፍል ተወሰነበት

በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ውስጥ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት የፈጸመ አንድ ግለሰብ በፅኑ እስራት ሲቀጣ፣ በግዴለሽነት በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ድርጅት ደግሞ የካሳ ክፍያ እንዲፈጽም መወሰኑን የኢትዮጵያኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
 
በየካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ ኪዳነ ምህረት አካባቢ ከ3.8 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸውን የኤሌክትሪክ ኬብሎች፣ አልሙኒየሞችና መዳቦች ሰርቆ በማከማቸት ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል። የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን ህግ ቢሮ ጋር በመተባበር ባደረጉት ኦፕሬሽን የተያዘው ይህ ግለሰብ፣ ጉዳዩን በተመለከተው የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት የካ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ምስክሮችን ካዳመጠ በኋላ ጥፋተኛነቱ በመረጋገጡ በ6 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።
 
በሌላ በኩል፣ በዚሁ ክፍለ ከተማ ኬብሮን መድኃኒት ቤት አካባቢ በግንባታ ላይ ከሚገኝ ህንፃ 12ኛ ፎቅ ላይ የወደቀ የህንፃ መወጣጫ ዊንች በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብልና በትራንስፎርመር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በደረሰው አደጋ ምክንያት የኮንክሪት ፖልና ትራንስፎርመሩ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
 
ተቋሙ የተበላሹትን መሰረተ ልማቶች በመተካት አገልግሎቱን ለመመለስ 1 ሚሊየን 900 ሺህ በላይ ወጪ ማድረጉን አስታውቆ፣ የጉዳት ካሳ እንዲከፈለው በምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን ህግ ክፍል አማካኝነት ክስ መስርቶ ነበር።
 
መዝገቡን የተመለከተው የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት የካ ምድብ 2ኛ ፍ/ብሔር ችሎት ማስረጃዎችን መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።
 
በዚህም መሠረት ጉዳት ያደረሰው ድርጅት 1 ሚሊየን 959 ሺህ 783 ብር የጉዳት ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበታል። በአሁኑ ወቅት ተከሳሹ ድርጅት 250 ሺህ ብር የከፈለ ሲሆን፣ ቀሪውን ክፍያ ለመፈፀም በቀጠሮ ላይ ይገኛል ሲል የኢትዮጵያኤሌክትሪክ አገልግሎት በላከልን መረጃ ተናግሯል፡፡
 
ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *