የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው የፈረንጆች 2025 ዓመት ከክሪፕቶ ምንዛሬ እና ከሚዲያ ኩባንያዎች ስምምነቶች በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ማግኘታቸውን አዲስ የወጡ የመንግስት ሰነዶች አመልክተዋል፡፡
የአሜሪካ የመንግስት ስነ-ምግባር ቢሮ ይፋ ባደረገው የፋይናንስ መግለጫ መሠረት፤ትራምፕ ከቤተሰባቸው የክሪፕቶ ንግድ ሥራዎች እና ሜም ኮይን ሽያጭ ከ1.4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ አግኝተዋል።
ይህ አሃዝ ታድያ ትራምፕ ከአባታቸው ከወረሱት የሪል እስቴት ኢምፓየር የሚያገኙትን ገቢ የበለጠ ሆኖ ተገኝቷል።
በፎርብስ መጽሔት ግምት መሠረት የተጣራ ሀብታቸውን ከ2.4 ቢሊየን ወደ 6 ቢሊየን ዶላር አሳድጎታል ተብሏል።
ትራምፕ ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ አሜሪካን የዓለም የክሪፕቶ ዋና ከተማ ለማድረግ ስትራቴጂካዊ የክሪፕቶ ክምችት ማቋቋምን እና የቁጥጥር ህጎችን ማቃለልን ጨምሮ በርካታ ደጋፊ ፖሊሲዎችን አስተዋውቀዋል።
ሆኖም ግን ይህ አካሄድ በዲሞክራቶች ዘንድ ከፍተኛ ትችት እያጋጠመው ነው።
በተለይም እንደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ያሉ የውጭ ሀገራት በትራምፕ ቤተሰብ ክሪፕቶ ኩባንያ ላይ ያደረጉት ኢንቨስትመንት የአሜሪካን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል በሚል ሴናተሮች አስቸኳይ የፓርላማ ችሎት እንዲጠራ እየጠየቁ ነው ሲል አልጄዚራ ዘግቧል።
ሳራ ዮሐንስ
ሰኔ 24/2018 ዓ.ም
