የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በገነባው የላቀ የላቦራቶሪ አቅም አማካኝነት በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከስተው የነበሩትን የኤም-ፖክስ (M-pox) እና የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኞችን ሳይዛመቱ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቋል።
ተቋሙ ይህን ያሳወቀው የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ለጋዜጠኞችና ለኢንስቲትዩቱ ባልደረቦች ገለፃ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በሰጡት ገለፃ፣ ተቋሙ የዘረመል ትንተና በማካሄድ አዳዲስ በሽታዎችን የመለየት አቅሙን ማሳደጉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከቀበሌ ጤና ኬላ ጀምሮ እስከ ማዕከል ድረስ የተዘረጋ ጠንካራ የበሽታ ቅኝት ስርዓት መኖሩንና በቀን 36 የሚሆኑ በሽታዎችንና የጤና ኩነቶችን በቅርበት መከታተል የሚያስችል አቅም መገንባቱን አብራርተዋል። ይህም ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት ከማዕከል ብቻ ሳይሆን በየወረዳው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ያልተማከለ አሰራር መዘርጋቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሀገራችን ዘመናዊ የጤና አገልግሎት የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከፊታችን ሐሙስ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆዩ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ገልፀዋል።
ተቋሙ በመጀመሪያው የተፈሪ መኮንን ሆስፒታልነት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ከ100 ዓመታት በላይ በጤና ምርምር፣ በክትባት ምርትና በላቦራቶሪ አገልግሎት ከፍተኛ ስራ ሲሰራ እንደቆየ ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ መቶኛ ዓመቱ ሲከበርም ተቋሙ ያስመዘገባቸው ሳይንሳዊ ውጤቶችና የታሪክ ጉዞዎች ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።
አዲስዓለም አበበ
ሐምሌ 07/2018 ዓ.ም
