በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ መስፈርቱን ሳይሟሉ በቀሩ ህንፃዎች እንደየደረጃው ከብር ከ10 ሺህ ያላነሰ እንዲሁም ከ1 መቶ ሺህ ያልበለጠ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል ብሏል፡፡
በአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቴክኖሎጂ እና ምህንድስና ዘርፍ ሀላፊ አቶ ምህረቱ ደሳለኝ እንደገለፁት፤ ደንቡን የማስፈጸሚያ መመሪያ ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱን እና የመቅጣት ሂደት መጀመሩን ነግረዉናል።
የተቋማት ህንፃዎች የደህንነት ክትትል ስራዎች መስፈርቱን ባላሟሉ ነባር ህንፃዎች ጨምሮ ለአዳዲስ ህንፃዎች እስከ መቅጣት የሚያደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ያስረዳሉ።
የሚጠበቅባቸዉን የእሳት እና አደጋ ደህንነት መስፈርቶች እንዲሟሉ ለአዳዲስ ህንፃዎች ከግንባታ ጀምሮ ድጋፍ እና ምክር እንዲሁም ስልጠና እያደረግን ነዉ ያሉት ሀላፊዉ፤ ይሄን ባላሟሉ ላይ ግን ቅጣት እንደሚጣል ገልፀዋል።
ይህ አሰራር አዲስ ለሚሰሩት ህንፃዎች ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ሳያሟሉ የተገነቡትንም ጭምር የሚጠበቀዉን የአደጋ ደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ ስራዎች እንዳሉ ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
ህንፃዎች ደረጃውን የጠበቀ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያዎች እና እሳት መነሳቱን የሚጠቁሙ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ የአደጋ ጊዜ መዉጫዎችን እንዲያሟሉ ማድረግ ከመስፈርቶቹ ዉስጥ ይገኝበታል።
የዚህ ደንብ ትግበራ የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር በመሆን እንደሚተገበር ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ለዚህ ሀላፊነት እንደተሰጠዉ የነገሩን አቶ ምህረቱ፤ የክትትል እና ድጋፍ ስራ እንደሚሰሩበት ተናግረዋል።
አቶ ምህረቱ ኮሚሽኑ አደጋ ከመድረሱ በፊት ከግንዛቤ ጀምሮ እስከ ሰርተፍኬሽን ድረስ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ስራዎችን ጀምረናል ያሉት ሀላፊዉ፤ተቋማት የደህንነት ፍተሻ እንዲደረግላቸዉ ጥያቄ የሚያቀርብበት እና ክትትል የሚያደርግበት እንዲሁም የኮሚሽኑ ባለሙያዎች እንዲቆጣጠሩት የሚያደርግ ስርአት እንዳለ ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ ሕንጻዎች ላይ እሳት ቢያጋጥም በፍጥነት ለማጥፋት የሚያግዙ ዘመናዊ ስካይ ሊፍተር ማሽኖች በተጨማሪም የፋየር ትራክ መሣሪያዎች እንዳሉት ተገልጿል፡፡
ቁምነገር አየለ
ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም
